ቀጥታ፡

አዲሱ የአደረጃጀት መዋቅር ለከተሞች እድገትና ለተቀላጠፈ አገልግሎት ትልቅ ዕድል ነው

ጅማ፣ ጥቅምት 8/2019 (ኢዜአ)፡- አዲሱ የኦሮሚያ ክልል መዋቅራዊ አደረጃጀት አገልግሎትን በፍጥነት ለማግኘትና ለከተሞች እድገት ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን የሊሙ ኮሳ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ። 

ትልቅ ሀገር; ትልቅ ህዝብ; ታላቅ ርእይ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ፣ የቢሮክራሲ ሰንሰለቶችን ለመቀነስ እና የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማፋጠን በሚል አዲስ የመዋቅር ሪፎርም ትግበራ ላይ ይገኛል። 

በዚህ አዲስ አደረጃጀት ቀደም ሲል የነበሩ የሥልጣንና የአገልግሎት ውክልናዎች ወደ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌ የወረዱ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የክልሉ ዞኖች በየአካባቢያቸው በሚገኙ ነባራዊ ሁኔታዎችና በኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው መሠረት በትልልቅ ዓበይት ዞኖች እንዲዋቀሩ ተደርጓል።

በዚህ መሠረት በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን የሊሙ ኮሳ ወረዳም በአዲሱ አወቃቀር መሰረት የዞኑ የጸጥታ እና ሌሎች ተቋማት መቀመጫ ሆና መመረጧ ይታወሳል።

በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ ረሻድ ከማል (ዶ/ር)ን ጨምሮ የዞን እና የወረዳ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በሊሙ ኮሳ ወረዳ ተገኝተው የተለያዩ የልማት ዕንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።

በዚሁ ወቅት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የወረዳዋ ነዋሪዎች እንዳሉት አዲሱ የአደረጃጀት መዋቅር ለከተሞች እድገትና ለተቀላጠፈ አገልግሎት ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል።

በአዲሱ አደረጃጀት የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱ ወደ ሕዝቡ በመቅረቡ የቢሮክራሲ እንግልትን ያስቀረ፣ የመሠረተ ልማትና የከተሞች እድገት ውሳኔዎችን ያፋጠነ እንዲሁም ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥን ያሻሻለ መሆኑን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል አቶ እስክንድር ዩሐንስ እንደተናገሩት መዋቅሩ ለከተሞች ዕድገት ጉልህ ሚና አለው።

በተለይም ለዘመናት የሚገባትን ትኩረት ላላገኘችው የሊሙ ከተማ ይህ ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።  

በተለይም ከተማዋ የዞኑ የተለያዩ የፀጥታ እና የፍትህ ተቋማት መቀመጫ ሆና መመረጧ ትልቅ ደስታ እና ተነሳሽነት ፈጥሮብናል ብለዋል።


 

በተመሳሳይ አቶ ጉተማ ከድር እና አቶ ተስፋዬ ጌታቸው አዲሱ የክልሉ መዋቅር የአገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ ምቹ ከመሆኑም በላይ የህዝቡን ጊዜና ገንዘብ ይቆጥባል ብለዋል።


 

ከዚህ በተጨማሪም የተጓተቱ የመሠረተ ልማት ስራዎችን ለማጠናቀቅ ትልቅ እድል አለው ብለዋል።

የዞኑ አስተዳዳሪ ረሻድ ከማል (ዶ/ር )በበኩላቸው እንዳሉት፤ የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር መዋቅር ለውጥ የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ ሕዝቡ ለማቅረብ፣ የአስተዳደር ቅልጥፍናን ለማሳደግና የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን ወሳኝ አደረጃጀት ነው።


 

በተለይም የመንግሥት ዋና ዋና ሴክተሮች በአንድ ስፍራ ከመገኘት ይልቅ በተለያዩ ከተሞች መደራጀታቸው ሕዝቡ ለአገልግሎት የሚያደርገውን ጉዞና እንግልት ከመቀነሱም በላይ ጊዜና ወጪውን ለመቆጠብ ያስችላል።

ይህም የሕዝቡን ፍላጎት በቅርበት ለመረዳት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና የማኅበረሰቡን ጥያቄዎች በተሻለ ሁኔታ ለመመለስ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ፣ በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዲዳ ጉደታ፣ መዋቅራዊ ለውጡ በኢኮኖሚ የተጠናከረና ራሱን የቻለ ዜጋ ለማፍራት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።


 

መዋቅሩ በክልሉ ያሉ የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን ለመቅረፍ፣ የከተሞችን ዕድገት ለማጠናከርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አቶ ዲዳ አስረድተዋል።

የዞኑ የፀጥታ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጁኔዲ ኢማም በበኩላቸው መዋቅሩ የህዝቡን ሰላምና አንድነት ለማስቀጠል ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ ለተግባራዊነቱ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።


 

አመራሮቹ የመዋቅር ለውጡ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የሕዝብ ተሳትፎን በማጠናከር፣ የአስተዳደር ቅልጥፍናን በማሳደግና የልማት ሥራዎችን በትኩረት በማከናወን ለውጡን ከዳር ለማድረስ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም