ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወል እሴቶችን ማጎልበት ለሕዝብ አብሮነትና ልማት ወሳኝ ነው -ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)

ወልቂጤ፤ ጥቅምት 8/2019 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወል እሴቶችን ማጎልበት የሕዝቡን አብሮነትና ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለጹ።

"በመደመር መንግስት፣ የህዝብ ድምፅ፣ የጋራ ተሳትፎ፣ የጋራ ልማት!" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት የመደመር መንግስት ትላልቅ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች እውን በማድረግ ሁሉን አሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው። 

ለዚህም ሀገር በቀል እውቀቶችንና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን መሰረት ያደረጉ የመደመር ስትራቴጂዎችን ቀርጾ ወደተግባር መገባቱን አስረድተዋል።

የክልሉ መንግስትም የወል እሴቶችን ለሀገር እድገትና ሰላም መረጋገጥ አቅም በማድረግ ለህዝቡ አብሮነትና የጋራ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከቀደሙ አባቶች የወረስናቸው በጋራ የመስራት ባህልን በማስቀጠልና የመደመር እሳቤን በመተግበር የህዝብን ሰላምና ልማት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባው ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

የጉራጌ ህዝብም ለልማት የሚያደርገው ጠንካራ ማህበራዊ  መስተጋብር  የመደመር እሳቤ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በበኩላቸው እንዳሉት ዞኑ ያሉትን ፀጋዎች በመደመር መንግስት እሳቤ ለልማት በማዋል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አሰራር ዘርግቶ ወደ ተግባር ገብቷል።


 

በዚህም የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በመፍታት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  ብልፅግናን ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።

በመድረኩ የክልሉ የመንግሰት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)ን ጨሞሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም ከጉራጌ ዞኑ የተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም