ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሉ በሩብ ዓመቱ ከ35 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል

አርባ ምንጭ፤ ጥቅምት 8/2019 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ35 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትልና የሥራ ስምሪትና ገበያ ልማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ዘውዱ ሳሙኤል ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ከ285 ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊ ዜጎች የተለዩ ሲሆን በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም ከ35 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

ከእነዚህ ውስጥም 24 ሺህ የሚሆኑት የሥራ ዕድሉ በቋሚነት የተፈጠረላቸው ሲሆን ቀሪ 11 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሆኑ ናቸው።

እንደ አቶ ዘውዱ ገለጻ፣ ከሥራ ዕድል ተጠቃሚዎቹ መካከል ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑት የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ሆነዋል።

በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል የተፈጠረው በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማኑፋክቸሪግ እና በአገልግሎት የሥራ መስኮች መሆኑንም አመልክተዋል።

በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለሆኑ ዜጎች ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር የተመቻቸ ሲሆን ሰርተው ከሚያገኙት ገቢም 59 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እንዲቆጥቡ መደረጉንም ገልጸዋል።

ለዜጎች የአካባቢ ፀጋን ታሳቢ ያደረገ ክህሎት መር ሥራ ዕድል መፈጠሩን አቶ ዘውዱ ጠቅሰው፣ በመንግስት በኩል በገጠርና በከተማ 737 ሄክታር መሬት እና 79 ሼዶችን በማቅረብ ለመደገፍ ተችሏል ብለዋል።

የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል በአርባ ምንጭ ከተማ የ"ሂዊ ቪ" ባርና ሬስቶራንት ሰብሳቢ ሕይወት ዓለሙ ለአራት ሆነው በመደራጀት ሥራ መጀመራቸውን ገልጻለች።

ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ከመንግስት የክህሎት ስልጠና፣ 124 ሺህ ብር የገንዘብ ብድር እና የመስሪያ ቦታ እገዛ እንደተደረገላቸው አመልክታለች።


 

በማህበር ተደራጅተው በልብስ ስፌት ሥራ የተሰማሩት  የ"ሀዳስ ልብስ ስፌት ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ዘላለም ብርሃን በበኩሉ ማህበሩ በሦስት አባላት እና በሦስት የስፌት ማሽኖች ሥራ መጀመሩን ተናግሯል።

በመንግስት በኩል የመስሪያ ቦታ እና ሙያዊ የስልጠና ድጋፍ ማግኘታቸውን ገልጾ፣ ለተሻለ ለውጥና ተጠቃሚነት ጠንክረው እንደሚሠሩ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም