ቀጥታ፡

ለሀገራዊ መግባባት የሚረዱ ምክረ ሃሳቦችን ለመተግበር መንግሥት ዝግጁነቱን በይፋ መግለጹ ለውጤታማነቱ መሰረት ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2019 (ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ መግባባት የሚረዱ ምክረ ሃሳቦችን ለመተግበር መንግሥት ዝግጁነቱን በይፋ መግለጹ ለውጤታማነቱ መሰረት መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የተካሄደው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁ ይታወሳል። 

የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ዋና ዓላማና ግብ በሀገሪቱ የፖለቲካና ማህበራዊ ምህዳር ውስጥ ለዘመናት የዘለቁ ስር የሰደዱ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ላይ በሰለጠነ አግባብ  ዘላቂ ሀገራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ ምክረ ሀሳቦችን ማመንጨት ነው። 

በሂደቱም ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የዘለቁ ስብራቶችን በሀሳብ የበላይነትና በጥበብ መፍትሔ መስጠት እንደሚችሉ በተግባር አሳይተዋል። 

ምክክሩ በሕዝቦች መካከል ሀገራዊ አንድነትንና ወንድማማችነትን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል አዎንታዊ መንገድም አመላክቷል። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድነት ተሰባስበው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰፊው የመከሩበት ነው። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ አመለካከቶችና ልዩነቶች ቢኖሯቸውም ምክክር ለሀገሪቱ ዘላቂ እድገትና ሰላም እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ላይ የጋራ አቋም መያዛቸውን አውስተዋል።

በዚህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት ውስጥ 42 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በንቃትና በባለቤትነት መሳተፋቸውንም ተናግረዋል። 

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የነበሩ ታጣቂዎች መካከል ወደ ሰላማዊ መንገድ በመመለስ አጀንዳዎችን ያቀረቡ መኖራቸውን አስታውሰዋል።

የምክክር ሂደቱ የሁሉም ወገኖች ድምፅ የተሰማበት፣ አሳታፊነቱንና አካታችነቱን ያረጋገጠ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ መመዝገቡን አስገንዝበዋል።

የመንግሥት ተቀባይነትና ሕዝባዊ አመኔታ መጎልበት ለአንድ ሀገር ዘላቂ ሰላም፣ ማህበራዊ መረጋጋትና አጠቃላይ እድገት እውን መሆን መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል። 

ሀገራዊ መግባባትን ለማስፈንና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ምክረ ሀሳቦችን ለመተግበር መንግሥት ዝግጁነቱን ማስታወቁ ለውጤታማነቱ ትልቅ እርምጃ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሂደቱ የምክረ ሀሳቦችን የትግበራ ሂደት ለመከታተል የሚያስችል አጠቃላይ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን ፕሮፌሰር መስፍን ገልጸዋል።

የክትትልና ቁጥጥር ሥራው ስኬታማ ይሆን ዘንድ ምክር ቤቱ ከተለያዩ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት ጋር በቅንጅትና ትብብር እንደሚሠራ አንስተዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም