ቀጥታ፡

የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛል- ሸማቾች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2019 (ኢዜአ)፦ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ በማስቻላቸው፣ የኑሮ ውድነት ጫና በማቃለልና ገበያን በማረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኝ የተለያዩ ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለጹ።

የኅብረተሰቡን የእለት ተእለት የኑሮ ጫና ለማቃለልና የገበያ መረጋጋትን ለማስፈን መንግሥት እየወሰዳቸው ካሉ አበይት እርምጃዎች መካከል አንዱ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የማስፋፋት ተግባር ነው። 


 

ይህም አምራችና ደንበኛን በቀጥታ በማገናኘት፣ መሰረታዊ የፍጆታና የምግብ ምርቶች በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንዲቀርቡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛሉ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ሸማቾች የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ በየሳምንቱ አቅርቦቱ ሳይቋረጥ ተጠናክሮ መቀጠሉ የኑሮ ጫና በእጅጉ እንደቀነሰላቸው ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ቅድስት ሽመልስ እንዳሉት፤ ገበያው በአቅራቢያቸው ከተከፈተ ቆየት ማለቱን ገልጸው፣ በጥራትና በቅናሽ ዋጋ ምርቶችን ለማግኘት ማስቻሉን ተናግረዋል። 

ይህም የኑሮ ጫናን ከመቀነስ ባለፈ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ጨምሮ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ እመቤት ቢተው በበኩላቸው፤ የቅዳሜና እሁድ ገበያ በተለያዩ አካባቢዎች መኖሩ አቅመ ደካሞች ምርት ፍለጋ ርቀው እንዳይሄዱ ከማድረግ ባለፈ፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች አቅም ያማከለ መሆኑን ገልጸዋል። 

ገበያው የህዝቡን የኑሮ ጫና በማቃለል ረገድ ሰፊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አንስተዋል።


 

ወይዘሮ ተስፋ ሞገስ እና መጋቢ ሰለሞን ሲደልል በበኩላቸው የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በአቅራቢያቸው መኖሩ ልዩ ልዩ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት በማስቻል በኅብረተሰቡ ላይ የነበረውን የኑሮ ጫና በእጅጉ እያቃለለ ይገኛል ብለዋል። 


 

በገበያው የሚቀርቡት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከመደበኛው ጋር ሲነጻጸሩ በጥራትም ሆነ በዋጋ ልዩነት እንዳላቸው ገልጸዋል።


 

በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ምርቶቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ነጋዴዎች መካከል አቶ አበበ ዘውዴ እና ያሬድ በቀለ እንደገለጹት፣ ገበያው እየተለመደና ተመራጭ እየሆነ በመምጣቱ ጥራት ያላቸውን የተለያዩ ምርቶች ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። 


 

አክለውም የደላላን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ከገበሬው ተረክበው ማቅረባቸው የኅብረተሰቡን አቅም ባገናዘበ ዋጋ ተጠቃሚዎችን ማገልገል እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ እንደገለጹት፤ መንግሥት የኑሮ ውድነት ጫናን ለማቃለልና የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን አከናውኗል። 


 

በሰንበት ገበያዎች ምርቶችን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ጥራትን ማስጥበቅ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል።

ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ አምራቾች ምርቶቻቸውን በቀጥታ እንዲያቀርቡ በማድረግ፣ የሸቀጦች ዋጋ የኅብረተሰቡን አቅም ባማከለ መልኩ እንዲቀርብ የማድረግ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም