ቀጥታ፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዘመናዊ መልኩ የተገነባውን የቄራ አልማዝዬ ስፖርት ሜዳና ሥልጠና ማዕከልን አስረከቡ

አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 8/ 2019 (ኢዜአ) ፦ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዘመናዊ መልኩ የተገነባውን የቄራ አልማዝዬ ስፖርት ሜዳ እና ሥልጠና ማዕከልን ለስፖርት ቤተሰቡና ለወጣቶች በዛሬው ዕለት አስረክበዋል።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት እንዳሉት ይህ ሜዳ በታሪኩ ለኢትዮጵያ ኩራት የሆኑ ታዋቂ ስፖርተኞችን አፍርቷል። ዛሬም ከዚህ ሜዳ አዳዲስ የስፖርት ጀግኖች፣ የሀገር ኩራቶችና የድል ባለቤቶች እንዲፈልቁ እድሉን እየፈጠርን ነው።


 

ሜዳው ከዚህ ቀደም በአቧራና በጥሻ ተውጦ፣ ለስፖርት እንቅስቃሴ ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ቆይቶ ነበር። ዛሬ ግን በድጋሚ ለወጣቶቻችን፣ ለታዳጊዎችም አካታች ሆኖ ስለተገነባ የችሎታቸው መድረክና የሕልማቸው ተስፋ ሆኖ ተመልሷል።

በከተማችን የስፖርት መሠረተ ልማትን ማስፋታችን ለወጣቶችና ለታዳጊ ልጆች ጤናማ፣ ተስፋ የሞላበትና የስኬት መንገድ እየከፈትን መሆናችን ነው። ከዚህ ሜዳ በሀገርና በዓለም መድረክ የሚያበሩ ታላላቅ ስፖርተኞች ይፈልቃሉ የሚል እምነት አለን!

ይህ የጋራ ሀብታችን ነው። እንጠብቀው፣ እናልማበት፣ በጋራም እናሳድገው!

ለወጣቶቻችን ዕድል እንፍጠር፤ ለሕልማቸው መንገድ እንክፈት፤ ለኢትዮጵያም አዲስ የድል ታሪክ እንጻፍ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም