የስፖርት መሰረተ ልማቶች መጪውን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ በአዲስ መልክ እየተገነቡ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት መሰረተ ልማቶች መጪውን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ በአዲስ መልክ እየተገነቡ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 8/ 2019 (ኢዜአ) ፦የስፖርት መሰረተ ልማቶች መጪውን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ በአዲስ መልክ እየተገነቡ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የቄራ አልማዝዬ ስፖርት ትምህርትና ስልጠና ማዕከል መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
በዚህ ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳሉት የአልማዝዬ ሜዳ የስፖርት አፍቃሪውን ፍላጎት መሰረት በማድረግ እንደገና ተገንብቷል።
ማዕከሉ አካታች ሆኖ በብዙ መንገድ መለወጡን አንስተው የገቢ ምንጭ የሚሆኑ ሱቆችንና ክሊኒክን ጨምሮ የተለያዩ መገልገያዎችን የያዘ ነው ብለዋል።
የአልማዝዬ ሜዳ የቀድሞ ስመጥርና አንጋፋ ተጫዋቾችን ያፈራ መሆኑን አመልክተው፤ መጪውን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ በአዲስ መልክ መገንባቱን ተናግረዋል።
ለብሄራዊ ቡድን የሚበቁና በአፍሪካና በዓለም ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ በርካታ ታዳጊዎችን የሚያፈራ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
የከተማው አስተዳደር በ2019 በጀት ዓመት ከ150 በላይ የስፖርት ሜዳዎችን ለመገንባት ማቀዱንና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የስፖርት መሰረተ ልማት ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።