አርሰናል ከኖቲንግሃም ፎረስት እና ማንችስተር ዩናይትድ ከሊድስ ዩናይትድ : የዕለቱ ተጠባቂ መርሐ ግብሮች - ኢዜአ አማርኛ
አርሰናል ከኖቲንግሃም ፎረስት እና ማንችስተር ዩናይትድ ከሊድስ ዩናይትድ : የዕለቱ ተጠባቂ መርሐ ግብሮች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2019 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ላይ ኖቲንግሃም ፎረስት ከአርሰናል በሲቲ ግራውንድ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኖቲንግሃም ፎረስት በአምስት ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዟል። የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን አርሰናል በ15 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ባለሜዳው ፎረስት ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል። መርሐ ግብሩ ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርገው ነው።
በስድስተኛ ሳምንት ሊድስ ዩናይትድን 2 ለ 1 በመርታት ወደ አሸናፊነት የተመለሰው አርሰናል በድል ጉዞው ለመቀጠል ይጫወታል።
መድፈኞቹ ካሸነፉ ከሊጉ መሪ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ዝቅ ያደርጋሉ።
በሌላኛው መርሐ ግብር ሊድስ ዩናይትድ ከማንችስተር ዩናይትድ በኢላንድ ሮድ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ባለሜዳው ሊድስ በዘጠኝ ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ማንችስተር ዩናይትድ በስድስት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሊድስ ዩናይትድ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች፣ ማንችስተር ዩናይትድ ደግሞ ባለፉት አራት የሊግ መርሐ ግብሮች ማሸነፍ አልቻሉም።
ሁለቱ ክለቦች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌሎች መርሐ ግብሮች ብራይተን ከክሪስታል ፓላስ እና ቦርንማውዝ ከሰንደርላንድ በተመሳሳይ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።