ቀጥታ፡

መቻል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ: የዕለቱ ተጠባቂ መርሐ ግብር

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 8/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።

ከቀኑ 9 ሰዓት መቻል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በመጀመሪያ ሳምንት መርሐ ግብር መቻል ሃዋሳ ከተማን 1 ለ 0 ሲረታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወቅቱን ሻምፒዮን ሲዳማ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል።

መቻል በሶስት ነጥብ ስድስተኛ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተመሳሳይ ሶስት ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።

ሁለቱ ክለቦች በጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቡድኖች በ2018 ዓ.ም በሊጉ እርስ በእርስ በተገናኙባቸው ጨዋታዎች መቻል ድል በማድረግ ስድስት ነጥቦችን ወስዷል።

ሌላኛው መርሐ ግብር ሀዲያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በሆሳዕና አብዩ ኤርሳሞ ስታዲየም ያገናኛል።

ሀዲያ ሆሳዕና በመጀመሪያ ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ የ1 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል።

ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ከፋሲል ከነማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ያለ ምንም ነጥብ 16ኛ ደረጃን ሲይዝ ወላይታ ድቻ በአንድ ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቡድኖቹ በሊጉ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።

ባለፈው ዓመት በሊጉ ባደረጓቸው የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ሁለቱ ቡድኖች በተመሳሳይ አንድ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም