ኢትዮጵያ የምታገኘውን የልማት ፋይናንስ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ዕድሎች ለመቀየር ቁርጠኛ ናት- እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የምታገኘውን የልማት ፋይናንስ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ዕድሎች ለመቀየር ቁርጠኛ ናት- እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 8/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከአጋር አካላት የምታገኘውን የልማት ፋይናንስ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ዕድሎች ለመቀየር ቁርጠኛ መሆኗን የብሔራዊ ባንክ ገዢ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለፁ።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና በዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን "የተሻሉና ብዙ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር አፈጻጸምን ማፋጠን" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የሚኒስትሮች የክብጠረጴዛ ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።
በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር ያላትን አጋርነት መሠረት በማድረግም የልማት ውጤቶችን ለማፋጠን የፕሮጀክቶችን ዝግጁነት ለማሻሻል እንደምትሰራ ጠቁመዋል።
እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ የምታገኘውን የልማት ፋይናንስ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ዕድሎች ለመቀየር ያላትን ቁርጠኝነትም አብራርተዋል።
እንዲሁም የፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ሂደትን በማቃለል እና ሙያዊና ተቋማዊ አቅምን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢው አክለውም ፣የልማት ፋይናንስ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ድህነትን በመቀነስና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ተጨባጭ የልማት ውጤቶች እንዲመዘገቡ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር በቅንጅት ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።