ቀጥታ፡

ሀገራዊ የልማት ግቦችን ከክልላዊ የመልማት አቅም ጋር በማስተሳሰር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል

ሀዋሳ፣ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ‎ሀገራዊ የልማት ግቦችን ከክልላዊ የመልማት አቅም ጋር በማስተሳሰር የህዝቡን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር) ገለፁ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ የቀረበውን የበጀት ዓመቱን የክልሉ መንግሥት ሥራ አስፈጻሚ አካላት ዕቅድ አስመልክተው ከሚዲያዎች ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም የክልሉ መንግሥት ሀገራዊ የልማት ግቦችን ከክልላዊ የመልማት አቅም ጋር በማስተሳሰር የክልሉን ሕዝቦች ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በእርሻ ዘርፍ የተሟላ የግብርና ኤክስቴንሽን ድጋፍ በማድረግ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩን የላቀ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራም አስረድተዋል።

በእንስሳት ሀብት ልማት የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የዝርያ ማሻሻል፣ የእንስሳት ጤናና የመኖ አቅርቦትን የማሳደግ ሥራዎች ትኩረት እንደሚሰጣቸው ጠቅሰዋል።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉን በማሳደግ ተኪ ምርቶችንና የኤክስፖርት ምርቶችን ለማስፋት፣ በተለይም ሀገር በቀል ኢንቨስትመንቶች እንዲበረታቱ ይደረጋል ብለዋል።

የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራን ውጤታማ ለማድረግ የክህሎት ሥልጠና እንዲሁም የብድር፣ የመሥሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦትን የማሟላት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።

የፍትሕ ሥርዓቱን የማዘመንና በዘርፉ የሕዝቡን ቅሬታዎች አድምጦ ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ሥራ ትኩረት እንደሚሰጠው ጠቁመዋል።

እንዲሁም የሕዝብ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ በመታገዝ፣ ቀልጣፋና የተገልጋዮችን እርካታ ያረጋገጡ እንዲሆኑ ተቋማትን የማጠናከርና አገልግሎቶችን ወደ ሕዝቡ የማቅረብ ሥራ ይጠናከራል ብለዋል።

ምክር ቤቱ በጉባኤው የአምስት ቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎችና አባላት ሹመትን ያጸደቀ ሲሆን፣ በመጨረሻም የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሥራ ዕቅድና በጀት በማፅደቅ አስቸኳይ ጉባኤውን አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም