ግብፅ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የጠቅላላው አፍሪካ ሀብት አድርጋ መቀበል ይገባታል - ኢዜአ አማርኛ
ግብፅ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የጠቅላላው አፍሪካ ሀብት አድርጋ መቀበል ይገባታል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ ግብፅ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የጠቅላላው አፍሪካ ሀብት አድርጋ መቀበል እንደሚገባት ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊ የፖለቲካ ሳይንቲስትና ጠበቃ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም ገለጹ።
የፖለቲካ ሳይንቲስትና ጠበቃ ፕሮፌሰር አለማየሁ እንደገለጹት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመላው የአፍሪካ ሀብት ነው።
በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሳን በርናርዲኖ መምህር የነበሩት ፕሮፌሰር አለማየሁ፤ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን የማልማት መብቷ በዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ እና በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ባለው የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ መታየት አለበት ብለዋል።
የዓባይ ውሃን አስመልክቶ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች ውስጥ ኢትዮጵያ እንዳልነበረች አስታውሰው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ባልተሳተፈችባቸው ውሎች ልትገደድ እንደማትችል አስገንዝበዋል።
ስለዚህ የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች ግብፅ በዓባይ ውሃ ላይ የምታነሳው ጥያቄ ከታሪክ ቅሪትነት ያለፈ ትርጉም እንደሌለው ተናግረዋል።
አክለውም ግብፅ የዓባይ ተፋሰስን የተቀየረ ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ ሁኔታዎችን እንድትገነዘብ አሳስበዋል።
የዓባይ ወንዝ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በዓለም አቀፍ ሕግ ሥር ያሉባቸውን ግዴታዎች እየተወጡ መብታቸውን በሚያከብሩ ህጎች መመራት አለባቸው።
የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አክትሟል፤ ግብፅም በዓባይ ላይ የቅኝ ግዛት ባለቤትነት መብት አለኝ ልትል አትችልም ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ የታሪክ ጥያቄዎች የኢትዮጵያን የልማት ምኞት ለመገደብ መሠረት መሆን እንደሌለባቸው ገልጸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዋናነት ኤሌክትሪክ ለማመንጨትና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለመደገፍ ታስቦ የተገነባ ትልቅ ኢንቨስትመንት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ግድቡ ለቀጣናው የኢኮኖሚ እድገት ሊያበረክተው በሚችለው አስተዋጽኦ መታየት እንዳለበት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከውሃ ኃይል የምታመነጨው ኤሌክትሪክ ለኢንዱስትሪ፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለግብርና ልማት እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጽኦ አለው።
ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ለጂቡቲ እና ለታንዛኒያ የምታደርገውን የኤሌክትሪክ ሽያጭ የቀጣናውን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር የኃይል መሠረተ ልማት ያለውን አቅም የሚያሳዩ ማረጋገጫዎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
የቀጣናው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና የልማት እንቅስቃሴ ካደገ ግብጽና ሱዳንን ጨምሮ በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ውስጥ ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድሎችን ሊፈጥር እንደሚችል አብራርተዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በርግጥም የአፍሪካ ሀብት ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ የፕሮጀክቱ አስፈላጊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ወሰን በላይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፕሮፌሰር አለማየሁ እንደገለጹት፤ ግብፅ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያሏት ስጋቶች በውይይት እና የተፋሰሱ ሀገራትን ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ በስምምነት መፍታት ትችላለች።
ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚመነጨው ኤሌክትሪክ ኃይል የቀጣናውን ልማት ለማፋጠን ያገለግላል።
የግብፅ መሪዎች የኢኮኖሚ ትስስርን ከመደገፍ ይልቅ ኢትዮጵያን ለማወክ ያለመ ፖሊሲ እየተከተሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግብፅ የተሳሳተ ፖሊሲ ከመከተል በመላው ቀጣናው ለጋራ ብልጽግና ከኢትዮጵያ ጋር የኢኮኖሚ ትብብር ማድረጉ አዋጪ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያን በወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ጫና ለማዳከም የሚደረጉ ሙከራዎች እንደማይሳኩም ገልጸዋል።
ግብፅ አካሄዷን በመመርመር ሰፊውን የአፍሪካ ቀንድ የሚጠቅሙ የልማትና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን መከተል እንደሚገባት ተናግረዋል።