ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአይበገሬነት ምስጢር - የምሉዕ ሉዓላዊነት ጉዞ

ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ ውስጥ የነፃነት፣ የጽናት እና የሰው ልጅ ኩራት ተምሳሌት ሆና የምትጠራ ታላቅ ሀገር ናት። የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደቷ አልጋ በአልጋ ሳይሆን በበርካታ ውጣ ውረዶች፣ ዘመናትን በተሻገሩ አብሮነትና መገፋፋቶች እንዲሁም የውጭና የውስጥ ጫናዎች ያለፈ ነው። ነገር ግን በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ሀገራዊ ሉዓላዊነቱን እና የግዛት አንድነቱን አሳልፎ ባለመስጠት በታሪክ ፊት ሁልጊዜም አንጸባራቂ ድል ጽፏል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አይበገሬነት በቃል ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን በደም እና በአጥንት የተረጋገጠ እውነት ነው። ከወረራዎች፣ ከጂኦ-ፖለቲካዊ ጫናዎች እና ከውስጣዊ የትግል ምዕራፎች በሻገር፣ እንደ ዓድዋ ባሉ ታላላቅ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት በአንድነት ቆመዋል። ኢትዮጵያውያንን የውጭ ወራሪዎችና ባንዳዎች ጥቃት የበለጠ አንድ ያደርጋቸዋል። ይህ ተግባራቸው በታሪካቸው የቀደሙ ምዕራፎች ሁሉ ተጽፎ የሚገኝ ነው። ይህ ቁርጠኝነትም ውዷን ሃገራችንን ኢትዮጵያን የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት አድርጓታል።

ዛሬ ላይ ዓለማችን የተወሳሰበ የፖለቲካ እና የቴክኖሎጂ ምኅዳር ውስጥ ትገኛለች። በመሆኑም የምትጋፈጣቸው ፈተናዎች እንደ ቀደመው ዘመን በመሳሪያ በሚደረግ ግልጽ ውጊያ ብቻ የተገደበ አይደለም። ይልቁንም የሕዝብን ሥነ-ልቦና ለማዳከም እና እርስ በርስ ለማጋጨት የሚነዙ ሐሰተኛ መረጃዎች፤ የሀገርን ሰላም ለማናጋት የሚደረጉ ድብቅ ስልቶች፤ በኢኮኖሚና በፖለቲካው የተደቀኑ ተጽዕኖዎች አዲሶቹ የትግል አውደ-ግንባሮች ናቸው።

እነዚህ አዳዲስ ዘመናዊ ፈተናዎች የሚጠይቁት ጥበብ፣ ትዕግሥት እና ጥልቅ አርቆ አሳቢነትን ነው። በዚህ የዘመናችን የፈተና ሂደት ውስጥ የሀገርን ጽናትና አይበገሬነት ለማስቀጠል የመንግሥት እና የሕዝቡ ጠንካራ አንድነት መኖር ወሳኝ ነው። በተለይም የወጣቱ ትውልድ አርቆ አሳቢነት ለነገዋ ኢትዮጵያ ሕልውና ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

ወጣቱ በመረጃ ጦርነት ውስጥ ሳይሸነፍ፣ የሐሰተኛ መረጃዎችን ዓላማ በመረዳት እና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ እውነታዎች ላይ በማተኮር ሀገሩን መጠበቅ አለበት። ስሜታዊነትን በማስወገድ፣ በውይይትና በምክንያታዊነት የሀገርን ዘላቂ ጥቅም ማረጋገጥ የወጣቱ ኃላፊነት ነው። አባቶች ሀገርን በደም ጠብቀው እንዳስረከቡ ሁሉ፣ የአሁኑ ትውልድም በዕውቀት፣ በሥራ፣ በቴክኖሎጂ እና በጽናት የሀገርን ሉዓላዊነት የማስከበር ሃላፊነት አለበት።

ለዚህ ነው የመደመር መንግሥት ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተጋ የሚገኘው። በመደመር እይታ ሉዓላዊነት ማለት የሀገርን ወሰንና ግዛት በመከላከያ ሰራዊት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ፣ የምግብ፣ የዲፕሎማሲ፣ የቴክኖሎጂ እና የስነ-ልቦና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥም ጭምር ነው።

ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት እና ወደ ውጭ መላክ በመጀመር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ በግብርናው ዘርፍ በሰብል፣ በእንስሳትና በጓሮ አትክልት ምርቶች ራስን የመቻል ሥራዎች እንዲሁም ምርታማነትን ማሳደግ፣ የፋይናንስ ዘርፉን ማዘመን እና የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚስቡ አሰራሮችን መዘርጋት የመደመር መንግሥት ምሉዕ ሉዓላዊነት አንጓዎች ናቸው።

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ምኅዳር ውስጥ የኢትዮጵያን ድምፅ ማጎልበት እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲን ማጠናከርም የኢትዮጵያን ጽናት እና አይበገሬነት ማስቀጠያ መንገዶች ናቸው። በሰላማዊ መንገድ እና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን በመከተል የሀገርን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ እና የደህንነት ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ የባህር በር ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶች ይጠቀሳሉ።

በሌላ በኩል ምሉዕ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ መንገዱ በሳይበር ዘርፍም የግድ መታገዝ ግድ ባለበት ዘመን ላይ እንገኛለን። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በማጠናከር ሀገሪቱን ከመረጃና ከሳይበር ጥቃቶች የመጠበቅ፣ እንዲሁም አዳዲስ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን የማልማት ሥራ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው።

ከሁሉም በላይ የመከላከያ ሰራዊቱን እና የደህንነት ተቋማትን በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች፣ በድሮን ቴክኖሎጂዎች፣ በሳይበር ደህንነት እና በሙያዊ ብቃት ማደራጀት ጊዜው የሚጠይቀው ነው። የመደመር መንግሥት ነባር የሰራዊቱን ክፍሎች ዓለም በደረሰበት ደረጃ ከማዘመን ሥራው ጎን ለጎን ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ የባህር ኃይል ግንባታ ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ ይገኛል።

በጥቅሉ ኢትዮጵያ የጽናትና የአይበገሬነት ምልክት ሆና የዘለቀችው በአጋጣሚ ሳይሆን፣ በሕዝቧ አስተዋይነት፣ በቆራጥነቱ እና ለሉዓላዊነቱ ባለው ጥልቅ ፍቅር ነው። የዛሬው ዘመን ፈተናዎች ቢወሳሰቡም፣ የመንግሥትና ሕዝብ የተቀናጀ ጥረት እንዲሁም የወጣቱ አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት ታክሎበት  ኢትዮጵያ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ፈተናዎችን አሸንፋ የጽናትና የነፃነት ምልክት ሆና መቀጠሏ የማይቀር ሀቅ ነው።

 

 

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር የሁሉም ተሳትፎ ያስፈልጋል - አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር የሁሉም ተሳትፎ ያስፈልጋል ሲሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ( ዶ/ር) ገለጹ።

የዓባይና ቀይ ባህር ስትራቴጂክ ፎረም ያዘጋጀው እና "ዓባይ፣ ቀይ ባህርና የጋራ ተጠቃሚነት" በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ( ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ዓባይና ቀይ ባህር የማይነጣጠሉ ናቸው።

ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ታሪካዊም ተፈጥሯዊ  መነሻ እንዳላት ጠቅሰው፤  በቀይ ባህር በኩል ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስታካሂድ መቆየቷን አንስተዋል። 

በቀይ ባህር ላይ ከጥንት ጀምር ወደቦችን አልምታ ስትጠቀም መቆየቷን አስታውሰው፤ ከአገሮች ጋርም የነበራትን ኢኮኖሚያዊ ትብብሮችንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

ቀይ ባህር የኢትዮጵያ የፀጥታ ዋስትና ሆኖ ለዘመናት ዘልቋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህም ታሪክ የሚያስረዳው እውነት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሴራ ከቀይ ባህር  እንድትርቅ መደረጉን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም መከበር የሁላችንም ተሳትፎ እንደሚፈልግ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ የጋራ ግንዛቤ መያዝ ወሳኝ ነው ያሉት አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ፎረሙ ያዘጋጀው ውይይት ወቅታዊ እና ጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል።

#ትልቅ_ሀገር ፣ #ትልቅ_ህዝብ ፣ #ታላቅ_ራዕይ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም