የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የህብረተሰቡን ተሳትፎ አበክረን እንጠቀማለን - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የህብረተሰቡን ተሳትፎ አበክረን እንጠቀማለን
ቦንጋ ፣ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የአመራሩን የመፈጸም አቅምና የህብረተሰቡን ተሳትፎ አበክረን እንጠቀማለን ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን ገለጹ።
«ማንሰራራት ለክልላችን ከፍታ» በሚል መሪ ሐሳብ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሄዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ ለዘመናት የሕዝቡ ጥያቄ የነበሩ የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ ይገኛሉ።
በቀጣይም የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን ፈጠራና ፍጥነትን በማከል መሥራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህም አመራሩ ከተለመደው አሠራር በመውጣት በቁርጠኝነትና በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
እያደገ የመጣውን የአመራሩን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም በተገቢው በመጠቀም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትጋት መሥራት እንደሚጠበቅም አብራርተዋል።
በተጨማሪም ተግባራትን በየሂደቱ እየገመገሙና በሁሉም መስኮች የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የሕዝቡን የተደመረ አቅም መጠቀም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
አመራሩ ሂደትን ከመገምገም ተላቆ በተጨባጭ በተገኘ ውጤት ላይ ማተኮር አለበት ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ ናቸው።
የተለያዩ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችን በጥራትና በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ተክሌ በዛብህ፤ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መቻል ላይ ሁሉም አመራር ተገቢውን ድጋፍ ማድረግና ተግባራትን በቁርጠኝነት መፈፀም እንደሚገባውም አሳስበዋል።
በቀረቡት ሰነዶች ላይ አስተያየት የሰጡት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ በበኩላቸው፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ውጤቶች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ ከሚፈለገው አንጻር ገና ብዙ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በቀጣይም የገበያ ትስስር መፍጠር፣ ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ላይ የአካባቢውን ጸጋ መሠረት ባደረገ መልኩ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በገቡት ውል መሠረት ወደ ሥራ ያልገቡ ኢንቨስተሮች ላይ እርምጃ መውሰድና በየአካባቢው ፍትሐዊ ልማትን ተደራሽ ማድረግ ላይ በልዩ ትኩረት መሠራት እንዳለበትም አመልክተዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ በበኩላቸው፤ የሕዝቡን ተሳትፎ ከፍ በማድረግና ያሉ ሀብቶችን በተገቢው ጥቅም ላይ በማዋል ተጠቃሚነታቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍ ለማድረግ እንሠራለን ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የተመዘገቡ ውጤቶችን እንደ መስፈንጠሪያ በመጠቀም የተጣለብንን ትልቅ አደራ እንወጣለን ያሉት ደግሞ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ተሰማ ናቸው።
በተለይ የከተሞች የልማት ሥራን በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን በትጋት እንደሚሠራም ገልጸዋል።