በሰመራ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ለነዋሪዎች ምቹ የኑሮ ከባቢን እየፈጠሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰመራ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ለነዋሪዎች ምቹ የኑሮ ከባቢን እየፈጠሩ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማትና ሌሎች የከተማ ማሻሻያ ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ለነዋሪዎች ምቹ የኑሮ ከባቢን እየፈጠሩ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።
አስተያየት ሰጪዎቹ፤ በከተማዋ ያለው አስተማማኝ የሰላም ሁኔታ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንዲጠናከሩ አጋዥ መሆኑንም ተናግረዋል።
በልማቱ ውስጥ የአፋርን ባህላዊ እሴቶች የሚያንጸባርቁ የከተማ ማስዋቢያ ሥራዎች መካተታቸውም ለሰመራ የተለየ ገጽታ እየሰጣት መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሰመራ ከተማ ነዋሪ ሉባ አሊ እንደገለጹት፤ የሰመራ የሰላም ሁኔታ መጠበቁና መረጋጋት መኖሩ የከተማዋን የልማት እንቅስቃሴ ለማስቀጠልና የነዋሪዎችን የኑሮ ምቹነት ለማሳደግ አስፈላጊ መሠረት ሆኗል።
በተለይም በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉት የኮሪደር ልማትና የከተማ ውበት ሥራዎች ሰመራን ይበልጥ ማራኪ እያደረጓት መሆኑን ጠቁመው፤ ለከተማዋ ውበት ከመጨመር ባለፈ ለነዋሪዎች የተሻለ የኑሮ አካባቢ እየተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።
ሌላኛው ነዋሪ መሐመድ ኑር ዓሊ በበኩላቸው፤ ልማቱ የከተማዋን ውበት ከማሳደጉም በላይ የአፋርን ባህላዊ እሴቶች የሚያንጸባርቁ የማስዋቢያ ሥራዎችን በማካተት ለሰመራ ልዩ ገጽታ እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ሰመራ የተለያዩ ብሔሮችና ማኅበረሰቦች በአብሮነት የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን ገልጸው፤ ይህንኑ ሰላማዊ አንድነት መጠበቅ ለልማት ሥራዎች ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በልማቱ የአካባቢው ነዋሪዎች በተለያዩ ሥራዎች መሳተፋቸው ለአካባቢው ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
ሌላኛዋ ወጣት ልዩሴት ቻላቸው በበኩሏ፣ በሰመራ የሚታየው የልማት እንቅስቃሴ ከተማዋን ይበልጥ ማራኪ እያደረጋት መሆኑን ገልፃለች።
በኮሪደሩ አካባቢ የሚገኙ የመዝናኛ ስፍራዎችና የሕፃናት መጫወቻ ቦታዎች ለቤተሰቦችና ለሕፃናት ከመዝናኛነት ባለፈ ለአዕምሯዊ እድገት ጠቃሚ መሆናቸውን አስረድታለች።
እንደ ነዋሪዋ ገለጻ፣ በኮሪደሩ ዙሪያ ተጨማሪ ካፌዎች፣ የንግድ ሱቆችና ሌሎች አገልግሎቶች ቢስፋፉ ለነዋሪዎች የመዝናኛ አማራጮችን ከማሳደግ ባለፈ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ ይችላሉ።
ሌላኛው ነዋሪ ካሳዬ አረጋይ በበኩላቸው፤ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች በተለይም ለእግር ጉዞና ለስፖርት የሚያገለግሉ በመሆናቸው ለነዋሪዎች ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ሰመራ የተለያዩ ብሔሮችና ማኅበረሰቦች በአብሮነት የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን ጠቁመው፤ ይህንን ሰላማዊ አብሮነት መጠበቅ ለቀጣይ ልማት መሠረታዊ መሆኑን አስረድተዋል።
ነዋሪዎቹ በሰመራ እየተከናወኑ ያሉ የከተማ ልማት ሥራዎች የኑሮ ምቹነትን ከማሻሻል ባለፈ ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች አዳዲስ ዕድሎችን እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰላም ሁኔታውን በመጠበቅና የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል ከተማዋን ይበልጥ ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።