ቀጥታ፡

የአማራ ክልል ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት ያለውን የማይናወጥ አቋም በሰልፉ አሳይቷል- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ):- የአማራ ክልል ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት ያለውን የማይናወጥ አቋም በዛሬ ሰልፍ በግልጽ ማሳየቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ የክልሉ ሕዝብ ዛሬ ባደረገው ከፍተኛ ትዕይንተ-ህዝብ እውነተኛና አንጡራ ፍላጎቱ ሰላም፣ የህግ የበላይነትና ልማት የተረጋገጠበት ሀገር እና ክልል መፍጠር መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።


 

በተጨማሪም ይህ ሰልፍ ሕዝቡ ለኢትዮጵያ አንድነት ያለውን የማይናወጥ አቋም በድጋሜ የገለጸበት አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያውያን አንድነታቸው ክብራቸው፣ ጀግንነታቸው መጠሪያቸው፣ ነጻነታቸው ደግሞ መለያቸው መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህ ነጻነት በየዘመኑ በነበሩት ትውልዶች በተከፈለ ክቡር መስዕዋትነት የተገኘ ድል መሆኑን አብራርተዋል።

አክለውም ዛሬም ቢሆን ታሪካችንን በሕብረት ጠብቀን፣ ነጻነታችንን አጽንተን፣ በልጆቿ ብርቱ ጥረት የበለፀገች፣ የተከበረችና የታፈረች ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ በጋራ መሥራት ይኖርብናል ሲሉ አስገንዝበዋል።


 

የክልሉ ሕዝብ ለሠላም መሥፈን እና ለሕግ የበላይነት መከበር ያለውን የፀና አቋም በሰለጠነ አኳኋን በአደባባይ ወጥቶ ላሳየው ከፍተኛ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የክልሉ ሕዝብ በተለያዩ አካባቢዎች በአደባባይ ወጥቶ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ለክልሉ ፀጥታ አካላት ተጋድሎ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሀገር መጽናት ላሳየው ከፍተኛ ድጋፍ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም