ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ተኪና ለወጪ ንግድ የሚሆን ምርትን በስፋት ለማቅረብ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል

ጎንደር፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦  በአማራ ክልል ተኪና ለወጪ ንግድ የሚሆን ምርትን በስፋት በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማስፋት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን  የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የወጪ ንግድና ተኪ ምርትን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሒዷል።


 

የቢሮ ሃላፊው ኢብራሒም መሀመድ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በክልሉ ለወጪ ንግድና ለተኪ ምርት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።

በክልሉ የጥራጥሬና የቅባት ሰብል እንዲሁም የማዕድን ሀብት በማልማትና የቁም እንስሳትን ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ግብአት በማቅረብና ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ምርቱን ከእርሻ እስከ መዳረሻው ድረስ ያለውን የንግድና ግብይት ስርአት በህግ በመምራት ለሀገር እድገት ለማዋል እየተሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

​የግብይት ስርአቱን በማዘመንና በማጠናከር ህገ ወጥ ደላሎች የሚፈጥሩትን ችግር ለማስቆም የተሰራው ስራ ውጤታማ መሆኑን አመልክተዋል።

የክልሉ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ  የግብአት አቅርቦትን በማሻሻል የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ነው።


 

በዚህም የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ባለፈው ዓመት ከነበረበት 65 በመቶ ወደ 70 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም ቀደም ሲል ከውጭ ሀገር  ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለመተካት ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን  አስረድተዋል።

​ግቡን ለማሳካትም የኃይልና የብድር አቅርቦት እንዲሁም መሰረተ ልማት ለማሟላት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

በክልሉ ከ630 በላይ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያመርቱና ከ37 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን በላይ ተኪ ምርት ለማምረት ታቅዶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

​የኤም.ኤስ.ኢ ቢዝነስ ግሩፕ የባህር ዳር ቀጠና ስራ አስፈፃሚ አቶ አበረ አበራ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመት ከ750 ሺህ ኩንታል በላይ የሰሊጥ፣ ማሾና አኩሪ አተር ለውጪ ገበያ ለመላክ ማቀዳቸውን ገልፀዋል።

በባህር ዳር በሚገኘው የዘይት ፋብሪካቸውም በቀን 200 ሺህ ሊትር ዘይት በማምረት ለህብረተሰቡ እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።


 

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ አዳነ ታከለ በበኩላቸው፤ በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚመረቱ ገበያ ተኮር ምርቶችን ከአርሶ አደሩ ለመረከብ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በመድረኩ የክልሉ የዘርፉ ኃላፊዎች፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ አምራቾችና ለውጭ ገበያ የሚልኩ ነጋዴዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም