ቀጥታ፡

በተጠባቂው የደርቢ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስን 2 ለ 1 ረትቷል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ በፍቃዱ ዓለማየሁ በ57ኛው እና ኦካይ ጁል በ75ኛው ደቂቃ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

አማኑኤል ኤርቦ በ82ኛው ደቂቃ የቅዱስ ጊዮርጊስን ብቸኛ ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጓል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጨረሻ ሰዓት አቻ ለመሆን ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በጨዋታው ማብቂያ ላይ የኢትዮጵያ ቡናዎቹ በረከት ወልደዮሐንስ እና በፍቃዱ አለማየሁ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ያሬድ የማነ በቀይ ካርድ ወጥቷል።

53ኛው የፕሪሚየር ሊጉ የደርቢ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል።

በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድላቸውን ያስመዘገቡት ቡናማዎቹ ደረጃቸውን ከ14ኛ ወደ 7ኛ ከፍ አድርገዋል።

በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድ ነጥብ ከነበረበት 9ኛ ደረጃ ወደ 13ኛ ዝቅ ብሏል።

በሶስተኛው ሳምንት መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና ከነገሌ አርሲ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም