ቀጥታ፡

በጉራጌ ዞን በበጋ የተቀናጀ የግብርና ስራዎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

ወልቂጤ ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦በጉራጌ ዞን ያሉ እምቅ አቅሞችን በመጠቀም በበጋ የተቀናጀ የግብርና ስራዎች ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ተግባር በትኩረት እንደሚከናወን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው «የተቀናጀ የግብርና ትጋት ለላቀ ምርታማነት!» በሚል መሪ ሐሳብ የ2019 የበጋ የተቀናጀ የግብርና ሥራዎች የንቅናቄ መድረክን በወልቂጤ ከተማ አካሄዷል።


 

በወቅቱም የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንደገለጹት፤ በዞኑ የበጋ የተቀናጀ ግብርና በሰብል፣ በእንሰት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ ይገኛል። 

በዞኑ ያሉትን እምቅ አቅሞች በመጠቀም በበጋ የተቀናጀ የግብርና ሥራዎች ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ተግባር በትኩረት እንደሚከናወንም ጠቅሰዋል።

የከርሰ ምድር፣ አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ግድቦችንና ሌሎችንም የውሃ አማራጮች በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን ኃላፊው ጠቁመዋል።

በዚህም በበጋ የተቀናጀ የግብርና ሥራ ከ240 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸው ከዚህም ከ800 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።

በተጨማሪም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን የማጠናከር እና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

የእንስሳት ዝርያን በማሻሻልና ጤናቸውን በመጠበቅ ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንዲሁም የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማጎልበት በትኩረት ይሠራል ብለዋል።


 

በዞኑ የአበሽጌ እና የቸሃ ወረዳዎች ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች አቶ አብዱልከሪም ናስር እና አቶ ጠቅልል አባድየ በበኩላቸው፤ በተቀናጀ የበጋ መስኖ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሳደግ በምግብ ራስን የመቻልና ገበያን የማረጋጋት ሥራው እንደሚጠናከር ገልጸዋል።

የበጋ መስኖ ግብርና ልማት የሰብል ዓይነቶችን በማስፋት፣ ለእንሰትና ለዘላቂ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው ያሉት ደግሞ የእኖር ወረዳ ግብርና ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልመጅድ ጀማል ናቸው። 

ለውጤታማነቱም ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን፣ የምርጥ ዘር እና የማዳበሪያ አጠቃቀምን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም