ቀጥታ፡

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የዲጂታል አሠራርን በመተግበር በዳኝነት አገልግሎት ተጨባጭ ውጤት አስመዝግበዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሠራሮችን  በመተግበር በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በመዝገብ አያያዝን እና በቀልጣፋ የዳኝነት ሥርዓት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገባቸውን የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንት ፉአድ ኪያር ገለጹ።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የ2019 በጀት ዓመት የችሎት መክፈቻ እና የ2018 በጀት ዓመት የስትራቴጂክ እቅድ አፈፃፀም የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ዳኞች እውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር ተካሂዷል።


 

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንት ፉአድ ኪያር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የፍርድ ቤቶችን ተደራሽነት፣ ተጠያቂነትና የሥራ ቅልጥፍና ለማሻሻል ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር የዋይፋይ ኢንተርኔትና የዳታ ማዕከል ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ የኢ-ፋይሊንግ እና የዲጂታል ፊርማ ሥርዓቶችም ተዘርግተዋል።

ከፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚተላለፉ መዝገቦች በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት መላክ መቻላቸው የሰው ንክኪን በመቀነስ የሥራ ቅልጥፍናን አሳድጓል።

በተጨማሪም የሽምግልና አገልግሎትን በማስፋፋት በአማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴ የሚፈቱ መዝገቦችን ቁጥር መጨመር ተችሏል።

በ2018 ዓ.ም 166 ሺህ 833 መዝገቦች የቀረቡ ሲሆን፣ ከ143 ሺህ በላይ መዝገቦች መፍትሔ ማግኘታቸው አስታውቀዋል።

የዳኝነት ጥራትን ለማሻሻል የተገልጋዮች እርካታ ጥናት እና የውሳኔዎች የድህረ-ኦዲት ግምገማ ተካሂዷል ብለዋል።

የፍርድ ቤቶች ከሌሎች ተቋማት ጋር ያላቸውን ቅንጅት ማጠናከር ሌላው የስትራቴጂክ ዘመኑ ውጤት መሆኑን አንስተው ፣ በሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደርና በአቅም ግንባታ ዙሪያ ከሚመለከታቸው የመንግሥትና የፍትሕ ተቋማት ጋር በትብብር መሠራቱን ገልጸዋል።

የዳኞች ነፃነት ለዳኞች ብቻ የተሰጠ መብት ሳይሆን ለሕዝብ ጥቅምና መብት የሚውል መሆኑን አስገንዝበዋል።

በቀጣዩ የስትራቴጂክ ዘመን የዳኝነት ውሳኔዎችን ጥራት ማሻሻል፣ የሥነ-ምግባር ችግሮችን መቅረፍ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል።


 

በመርሐ ግብሩ ላይ ተሸላሚ የሆኑት በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በለሚኩራ ምድብ ፍትሐብሔር ችሎት ዳኛ ጌዳወርቅ ይትባረክ ፣ ባለፈው ዓመት በርካታ መዝገቦችን በማስተናገድና በመወሰን የተሻለ የሥራ አፈጻጸም ማሳየታቸው ለሽልማቱ እንዳበቃቸው ገልጸዋል።

እንዲህ ያሉ ሽልማቶች የዳኞችን ትጋት በማወቅ ለድካማቸው ዋጋ ከመስጠት ባለፈ፣ ተነሳሽነታቸውን የሚያሳድጉና በየዓመቱ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ሌላኛዉ ተሸላሚ የሆኑት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ዳኛ ሮባ ቀጨም ፣የፍርድ ቤት ሥራ ከፍተኛ የሥራ ጫናና የመዝገቦች ብዛት የሚታይበት እንደሆነ ጠቅሰዉ፣ ሽልማቱ ለቀጣይ ሥራቸው ተነሳሽነትና ሕዝብን በላቀ ታማኝነት ለማገልገል አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም