በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕሮጀክቶችን ተደራሽ ለማድረግ ቅንጅታዊ ስራ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕሮጀክቶችን ተደራሽ ለማድረግ ቅንጅታዊ ስራ ይጠናከራል
ወልቂጤ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ግንባታቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና አዳዲሶችን በመገንባት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ ስራዎች እንደሚጠናከሩ ተመለከተ።
የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ከተጠሪ ተቋማት ጋር እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን በወልቂጤ ከተማ ገምግሟል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ እንደተናገሩት ፣ የክልሉን ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን በልዩ ትኩረት ለማከናወን ትኩረት ተሰጥቷል።
በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች ግንባታቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና አዳዲሶችን በመገንባት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ ስራዎች እንደሚጠናከሩ አመላክተዋል።
በየዘርፉ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ መንከባከብና መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል ።
የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቲዮስ ሉምበሶ በበኩላቸው፥ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የውሃ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅና አዳዲስ የውሃ አማራጮችን ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
በክልሉ በ2019 በጀት አመት በመንግስት፣ በአጋር አካላትና በህብረተሰብ ተሳትፎ ከ483 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርጉ 162 ፕሮጀክቶች እንደሚገነቡ ተናግረዋል።
በዚህም የክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ሽፋን ከ53 በመቶ ወደ 61 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ እንደሚል አመልክተዋል።
አማራጭ የሀይል አቅርቦትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ከ75 ሺህ በላይ የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በማህበራት አማካኝነት በማምረት ለማሰራጨት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቅሰዋል ።
እንዲሁም 250 የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ በመገንባት ለቤት ውስጥ መብራት እና ለሌሎች አገልግሎቶች ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ በተያዘው በጀት አመት በማእድን ልማት የስራ እድል በመፍጠር እና የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ግብ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱንም አመልክተዋል።
የንፁህ መጠጥ ውሃን በተለያዩ አካባቢዎች ለማድረስ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቴ ወልደማርያም ናቸው።
በዞኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማሳደግ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመድረኩ ላይ የክልል፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳ እና የከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።