ቀጥታ፡

 ከሀላላ እስከ ጌጫ የዘለቀ የምድር ጌጥ

ሚዛን አማን፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ከሀላላ እስከ ጌጫ የዘለቀ የምድር ጌጥ

በቀደሰ ተክሌ- ሚዛን አማን

ብዝሃ ተፈጥሮ ለአንድ ሀገር ሀብት ከመሆንም አልፎ የዕድገት መሰላል ነው። የተፈጥሮ ሀብት የሌላት ሀገር አስተማማኝ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ገንብታ ዕድገቷን ልታረጋግጥ አትችልም። ከውሃ አካላት እስከ ማዕድናት፣ ከለም አፈር እስከ ደን ሀብት ያሉ ተፈጥሮዎች የሀገር ማንነት ትእምርት እስከ መሆን የሚደርሱ ስጦታዎች ናቸው። እነዚህ ተፈጥሮ የምትቸራቸው ሀብቶች ጥቅም የሚኖራቸው ደግሞ በተገለጠ ዐይን ተመልክቶ ከእጅ ጋር ማገናኘት ሲቻል ነው። ሀገራችንም በዘርፉ ያልተነካ አንጡራ ጸጋዎችን በተለያዩ አካባቢዎች ሸሽጋ ይዛለች።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሰፊ የደን ሽፋን የሚታወቅ የሀገራችን ክፍል ነው። ከሰው ንኪኪ የፀዳ ተፈጥሮ የሚገኝበት ይህ አካባቢ በባዮስፌር የተከለሉ የደን ክልሎችም የሚገኙበት ነው። ይህ ማለት የዓለም ዐይን ማረፊያ ከሆኑ የኢትዮጵያ ሀብቶች አንዱ ነው ማለት ነው። 

ይህ ደን የከበበው ጸጋ ብዙ ነው። ቀን ከሌሊት፣ በጋ ከክረምት የሚፈሰው የውሀ አካል ማኅደርም ነው። ከዐለቱ አናት ቁልቁል እየተምዘገዘጉ የሚወረወሩ እንደ ባርታ ያሉ ፏፏቴዎችን ከሀላላ እስከ ጌጫ መቁጠር ይቻላል።  በሰው ሰራሽ ጥበብ ተንጣለው የተቀመጡ የቤንች ሸኮው ደንቢና የሸካ ዞኑ ጋንዶች ሀይቆች ደግሞ በደን ታጥረው በአእዋፋት ዝማሬ ታጅበው የሰውን መንፈስ የሚያድሱ የተፈጥሮ ገጸ በረከቶች ናቸው። ሀይቆቹ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙ ፏፏቴዎች የታጀቡ ናቸው።

የኮንታው ጨበራ ጩርጩራና የምዕራብ ኦሞ ዞኑ ኦሞ ብሔራዊ ፓርኮች የዝሆን፣ የጎሽና ሌሎች የዱር አራዊት መናገሻዎች ናቸው። በፓርኮቹ አራዊት የሚፈልጉትን እየተመገቡ ከወንዙ እንደ ልባቸው እየጠጡ እንዲኖሩ ከጥንት ጀምሮ ተጠብቆ የቆየው የተፈጥሮ ደን ጉልህ ሚናን ተጫውቷል። ጦጣና ጉሬዛ በምድር የመመላለስ ያህል ከአንዱ ዛፍ ወደ ሌላው እየዘለሉ ቡረቃቸውን ሳያቆሙ ዘመናቸውን ያሳልፋሉ።

እልፍ አእዋፋትና የዕጽዋት ዝርያዎች መፍለቂያ የሆነው የተፈጥሮ እምቅ ደን በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በኩታ ገጠም ተንሰራፍቶ ከነ ክብሩ የምድር ጌጥ ሆኖ ይታያል። 

ደን የተፈጥሮ አየር ንብረት ሚዛን ከመጠበቅም በላይ ሰፊ ትርጉም አለው። የሀገር ኩራት፣ በዓለም መድረክ መድመቂያም ነው። ኢኮኖሚያዊ ትርጉሙ ደግሞ የሀገር የብልጽግና ተስፋ የምግብና መጠጥ ዋስትና ነው።  የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ደንን የተፈጥሮ አየር ንብረት ሚዛንን በማስጠበቅ እርጥበትን በማቆየት ከሚያስገኘው ተዘዋዋሪ ፋይዳ ባሻገር ደኑ የከበባቸው ሌሎች ሀብቶች ቀጥተኛ ገቢ የሚያስገኙ ናቸው።

ለአብነትም በክልሉ አብዛኛው የቡና ልማት በደን ውስጥ የሚገኝ ነው። በዓመት ከ60 ሺህ ቶን በላይ ጥራት ያለው ቡና ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርብበት የቡና ማሳ በደን የተከበበ ነው። ደን ከሌለ ቡና የለም ብለው የሚያምኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በጥምር እርሻ ዘዴም የታወቁ ናቸው።

በዓለም አቀፍ ገበያ ውድ የተባሉ የቅመማ ቅመም አይነቶች በስፋት የሚገኙት በደን ውስጥ ነው። የክልሉ ነዋሪዎች በደን ጥበቃ ባህላዊ ሥርዓታቸው ያቆዩት ይህ እምቅ ደን ኮረሪማ፣ ጥምዝና ሌሎች የተፈጥሮ ቅመሞች የሚበቅሉበት የአካባቢው አርሶ አደር የኢኮኖሚ ዋልታ ነው። ክልሉ በአማካይ ከ54 ሺ ቶን በላይ ምርት ከዚሁ ዘርፍ በየዓመቱ ለማእከላዊ ገበያ ያቀርባል።

በዓመት ከ70 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርብበት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ደን የንብ መንጋ መናኸሪያ ሆኖ ያገለግላል። ደን ውስጥ ገባ ብሎ ቀና ያለ ሰው ንቦች በአፉ ዙሪያ የሚጫወቱበትን ባህላዊ ቀፎ በቅርብ ርቀት መመልከት የተለመደ ነው። ከዚህ የሚመረተው የጫካ ማር በጣዕሙ የተሻለ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ገበያ ተመራጭ ነው። በዘመናዊ መንገድ በጓሮ ከሚሠራው የማነብ ሥራ ባሻገር በጫካ ማር ማምረት ልምዱ ያላቸው ዛሬም ቆንጆ የማር እሸት በየጊዜው እየቆረጡ ለገበታም ለገበያም ያውላሉ።

በክልሉ ውስጥ የሚገኘው ሁለት የደን ስፍራዎች በባዮስፌር ጥብቅ የደን ስፍራነት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት የተመዘገቡ ናቸው። ደኑ የሚጠበቀው የአካባቢው ማኅበረሰብ ለዘመናት ባካበተው ደን የመጠበቅ ሀገር በቀል እውቀትና እሴት ነው። እንደ "ኮቦ" እና "ጉዶ" ያሉ የደን ጥበቃ ባህላዊ ሥርዓቶች ደግሞ ዛሬም ተግባራዊ የሚደረጉ የካፌቾና ሸካቾ የጥንት ሥርዓቶች ናቸው።  ባህላዊ የደን ጥበቃ ሥርዓት ለደኖች ሕልውና መጠበቅ ዛሬም ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ማረጋገጫው ደግሞ በዩኔስኮ ከተመዘገቡ ደኖች እኩል አቅም ያላቸው የደን ክልሎች መኖራቸው ነው። ለአብነትም በቤንች ሸኮ ዞን ውስጥ በእግዜር ድልድይ እና ዑሲቃ ፍል ውሀ ያጌጠው የሸኮ አሞራ ገደልና የሼይ ቤንች ደን ተጠቃሽ ነው።

ለክልሉ ሕዝብ ደን የሕይወት ቅመም ነው። ይወዱታል፣ ይንከባከቡታል፣ ይጠብቁታልም። የዚህ ተግባራቸው ውጤት ደግሞ ዓመቱን በሙሉ ዝናብ ስለሚያገኙ፣ ወንዞቻቸው አይደርቁም የማሳቸው ምርት አይጠወልግም። ይህ በእንዲህ እንዳለ የመደመር መንግስት ዐይን ገላጭ የሆነ ኢኒሼቲቭ ይዞ መምጣቱ ተጨማሪ የተጠቃሚነት ዕድልን ከፍቷል።

ደን የከበበው ጸጋ ብዙ ነው፤ ያን አውጥቶ መጠቀም የሚያስችል መነጽር ደግሞ የቱሪዝም ልማት ነው። ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አምዶች አንዱ ቱሪዝም እንደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ባሉ አካባቢዎች ለዘመናት የተሸሸጉ ሀብቶችን ወደ ገበታ እያወጣ ነው። ለዚህም እንደ ሀላላ ኬላ፣ ዳና እና ደንቢ ሎጆችን ማንሳት ይቻላል።  በመደመር መንግሥት የተገነቡ እነዚህ ሎጆች በክልሉ ደን ከውሃ ጋር ያለውን ትስስር እሴት ጨምሮ ዓለምን ያስደነቀ መዳረሻ ማድረግ የተቻለባቸው ፕሮጀክቶች ናቸው። 

ተፈጥሮ በጥበብ ሲያጌጥ አየር ብቻ ሳይሆን ገንዘብ ይለግሳል። የአራዊት መመላለሻ ብቻ የነበሩ ጎዳናዎች ብርሃን ለብሰው ልማት ተጎናጽፈው የሰው ልጅ መመሰጫና መዝናኛ መሆን ችለዋል። በአንድ በኩል የውጭ ምንዛሬ በቀጥታ የሚገኝባቸው በሌላ በኩል ደግሞ የሥራ ዕድል ለወጣቶች ተፈጥሮ የእለት ጉርስ የወር ቀለብ የሚገኝባቸው ሆነዋል። ይህ ሲሆን አሁንም የተፈጥሮ ጸጋው በደን እንደተከበበ መሆኑ ደግሞ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ብቻ ሳይሆን ሦስት አራት ወፍ እንደመምታት ያህል ነው የሆነው።

ተፈጥሮን እያደነቁ ራስን ማዳመጥ ለሚሹ ሁነኛ የሆኑ እነዚህ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የገበታ ፕሮጀክቶች በአቅራቢያቸው በርካታ ባህላዊና የተፈጥሮ መስህቦችን ያቀፉ ናቸው። የመደመር መንግስት እነዚህን ሀብቶች ጥቅም ላይ ለማዋል ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ጉዳዮችን አቅዶ እያሟላ ይገኛል። ለምሳሌ በክልሉ ምንም አይነት አገልግሎት የሚሰጥ የአውሮፕላን ማረፊያ ያልነበረ ሲሆን አሁን የሚዛን አማን አይሮፕላን ማረፊያ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየሰጠ ነው።

የገበታ ፕሮጀክቶች ተገንብተው በአካባቢው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን በዞን እና በከተማ ደረጃ መገንባት የሚቻልበትን በር ከፍተዋል። ለአብነትም በካፋ ዞን የእግዜር ድልድይ መዳራሻና የሸካ ዞንን የጋንዶች ሀይቅ መንገድ ግንባታን ማንሳት ይቻላል። በሁሉም ዞኖች በወረዳ ጭምር አንድ አንድ መዳራሻ በራስ አቅም የማልማት ንቅናቄ ተጀምሮ ማየት ተችሏል። ይህ ትልቅ መነቃቃት ነው። ደንን የከበበውን ጸጋ ወደ ኢኮኖሚያዊ ትርጉም በመቀየር የሕዝብ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚቻል የሚያሳዩ ጅምር ተግባራት ናቸው። የክልሉን ያልተነኩ የተፈጥሮ ሀብቶች በየጊዜው እያለሙ ገሀድ የማውጣቱና ጥቅም ላይ የማዋሉ ጉዳይ መጠናከር አለበት። ሰላም!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም