ቀጥታ፡

በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተከናወነ ያለው ተግባር ውጤት እያመጣ ነው

አሶሳ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም በመሸፈን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ያለው ተግባር ውጤት እያመጣ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አመራሮች እና ባለሙያዎች በክልሉ በአቡራሞ ወረዳ ከ40 ሄክታር በላይ መሬት ላይ እየለማ የሚገኘውን የአኩሪ አተር ሰብል ተመልክተዋል።

የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሐመድ አብዱላዚዝ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ መንግሥት ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም በመሸፈን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና ተረጂነትን ለመቀነስ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።

ኢንሼቲቩ ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን በማልማት ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።


 

ኮሚሽኑ በዘንድሮው ዓመትም በቆሎ፣ አኩሪ አተር እና የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን በሦስት የእርሻ ማዕከላት ላይ እያለማ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በክልሉ ተረጂነትን በራስ አቅም የመሸፈን አቅም እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በአቡራሞ ወረዳ የሚገኘው የአኩሪ አተር እና የበርበሬ ሰብል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እና በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ በጥሩ ሁኔታ እየለማ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

ክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በራሱ አቅም ድጋፍ ማድረግ መጀመሩን ጠቅሰው፣ ከእርሻ ማሳው ጎን ለጎን ለኮሚሽኑ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን እያለማ መሆኑን አመላክተዋል።

ኮሚሽኑ በዘንድሮው ዓመት ከ300 ሄክታር በላይ ማሳ ላይ የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን እያለማ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ተረጂነትን ለመቀነስ እየተከናወኑ ከሚገኙ የግብርና ሥራዎች ባሻገር የሀብት ማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም