በክልሉ ግብርናውን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ግብርናውን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል
ደሴ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ግብርናውን በማዘመንና ምርታማነትን በማሳደግ መንግሥት ለሕዝብ የገባውን ቃል ወደ ተግባር ለመለወጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገለፁ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ በኮምቦልቻ ባካሄደው የንቅናቄ መድረክ ላይ በዘንድሮው በጋ በመስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥ ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በአዲስ የሚለማ መሆኑም ተገልጿል።
በመድረኩም ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በክልሉ ግብርናውን በማዘመንና ምርታማነትን በማሳደግ መንግሥት ለሕዝብ የገባውን ቃል ወደ ተግባር ለመለወጥ እየተሠራ ይገኛል።
ለዚህም በተለያዩ ዞኖች ያለውን የመልማት አቅምና ጸጋዎች በመጠቀም ቀጣይነት ያለው ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ግብ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
አክለውም በምሥራቅ አማራ ያለውን ሰፊ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃ በመጠቀም ለአካባቢው ተስማሚ የሆነውን የፍራፍሬና የአትክልት ልማት በስፋት ለማካሄድ ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል።
በኩታ ገጠም (ክላስተር) የተጀመረውን የፍራፍሬ ልማት በማስፋት የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት በተጨባጭ ለማሳደግ የክልሉ መንግሥት ርብርብ እያደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
ክልሉ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ትርፍ ምርት በስፋት ለገበያ እንዲያቀርብ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግም ተናግረዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መስፍን አበጀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ ያለውን በመስኖ የመልማት አቅም በመጠቀም ቢያንስ አንድ አርሶ አደር አንድ የመስኖ አማራጭ እንዲኖረው ግብ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በምሥራቅ አማራም ያለውን ተስማሚ የአየር ንብረትና የውሃ አቅም በመጠቀም ለአትክልትና ፍራፍሬ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ወደ ትግበራ መገባቱን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ቴክኖሎጂንና አዳዲስ አሠራሮችን በመጠቀም ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሰብሎችን በስፋት ለማልማት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ በያዝነው በጋ ከሚለማው ከ734 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ከ250 ሺሕ ሄክታር በላይ መሬት አዲስ በመስኖ የሚለማ መሆኑንና 400 ሺህ ሄክታር የሚሆነው ደግሞ በበጋ ስንዴ የሚሸፈን መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህም አጠቃላይ የበጋ መስኖ ልማት ከ95 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደመቀ አድማሱ በበኩላቸው፤ በዞኑ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በኩታ ገጠም ለማልማት ሥራ ልዩ ትኩረት መሠጠቱን ተናግረዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀማል አሊ በበኩላቸው፤ በዞኑ በመስኖ ከሚለማው ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
በዚህ የንቅናቄ መድረክ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አመራሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።