የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሽንፈት አስተናገደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሽንፈት አስተናገደ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ከዩጋንዳ አቻው ጋር ባደረገው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ 4 ለ 0 ተሸንፏል።
በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዩሱፍ ሴንዮንጋ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አርኖልድ ካዬምባ እና ኡካሻ ጄምባ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
የዩጋንዳ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ብልጫ ወስዶ ተጫውቷል።
ውጤቱን ተከትሎ በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በቀጥታ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድሉ አልተሳካም።
ቀይ ቀበሮዎቹ ማክሰኞ ጥቅምት 10 2019 ዓ.ም በሚያደርጉት የደረጃ ጨዋታ ካሸነፉ ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ።
ዩጋንዳ በአፍሪካ ዋንጫው ሴካፋን ወክላ የምትሳተፍ የመጀመሪያ ሀገር መሆኗን አረጋግጣለች።
በሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር አዘጋጇ ሩዋንዳ ከሶማሊያ ጋር ከቀኑ 10 ሰዓት ከ30 ላይ በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ትጫወታለች።
በውድድሩ ላይ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የሚወጡ ሀገራት የሴካፋ ዞንን ወክለው እ.አ.አ በ2027 በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 17ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ።
በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ራሷን ሞሮኮ ጨምሮ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።