በድሬዳዋ የነዋሪዎችን የልማት ጥያቄዎች በተቀናጀ መንገድ የመፍታት ጥረት ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ የነዋሪዎችን የልማት ጥያቄዎች በተቀናጀ መንገድ የመፍታት ጥረት ይጠናከራል
ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የነዋሪዎችን የልማት ጥያቄዎች በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አብዱላሂ አደን ገለጹ።
የድሬዳዋ አስተዳደር የተቋማት የመጀመሪያ ሩብ በጀት አመት የስራ ዕቅድ አፈፃፀም ዛሬ ተገምግሟል።
በግምገማው ላይ በገጠርና በከተማ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች የታቀዱ ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በተቀናጀ መንገድ ለመተግበር የተጀመሩ ጥረቶች አበረታች መሆናቸው ተመልክቷል።
ውይይቱን የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አደን በወቅቱ እንዳሉት፤ የነዋሪውን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተቀናጀ እና በተናበበ መንገድ ለመፍታት በበለጠ ትጋት ይሰራል።
በዘንድሮ በጀት አመት የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ጠቁመው በተለይም የስራ አጥነት ችግርን የመፍታት ስራ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን አመልክተዋል።
በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በመጠጥ ውሃና በመስኖ ዘርፎች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትጋት እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።
በአስተዳደሩ የሚፈለገውን ለውጥና ውጤት ለማስመዝገብ ገቢን በተቀናጀ መንገድ ለመሰብሰብ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም ገቢን አሟጦ የመሰብሰብና የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኘው አመራር መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው በአስተዳደሩ የስራ ጥያቄዎችን ለመፍታት የተጀመሩ ስራዎች እንደሚጠናከሩ አመልክተዋል ።
የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የምርት አቅርቦትን በስፋትና በጥራት ተደራሽ የሚያደርጉ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በየደረጃው የሚገኘው አመራር የተሰጠውን ተልዕኮ በቁርጠኝነት ለመወጣት መትጋት እና የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንዳለበት አሳስበዋል ።
በተለይ ገቢን አሟጦ የመሰብሰብና የነዋሪዎችን መሠረታዊ ጥያቄዎች በላቀ ደረጃ ለመፍታት ትልቅ ኃላፊነት እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።