መንግስት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው የልማት ግቦች እንዲሳኩ የበኩላችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው የልማት ግቦች እንዲሳኩ የበኩላችንን እንወጣለን
ወራቤ ፤ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ) ፦ መንግስት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ የያዛቸውን የልማት ግቦች ለማሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስልጤ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
የክልሉ መንግሥት በቀጣይ ለማከናወን በያዛቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶች ዙሪያ ከወራቤ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ዛሬ የምክክር መድረክ አካሄዷል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙ የወራቤ ከተማ ነዋሪዎች፣ መንግስት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው የልማት ግቦች እንዲሳኩ የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ ሩቂያ አብደላ እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት የያዛቸው የልማት ዕቅዶች ተጨባጭ ውጤት የሚያስመዘግቡ ናቸው።
በመሆኑም ሕዝቡ በምርጫ ድምፁን በመስጠት ለአሸናፊው ፓርቲ አለኝታነቱን እንዳረጋገጠ ሁሉ፣ አሁንም በቀጣይ ዓመታት ለመተግበር የተያዙት የልማት ግቦች እንዲሳኩ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
አክለውም፣ መንግሥት ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያደርሱ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉም ገልጸዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ነስሬ አብደላ በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት የያዛቸው የልማት ግቦች ለተተኪው ትውልድ የሚተላለፉና ዘመን ተሻጋሪ የልማት ሥራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን ከማቅረብ በተጨማሪ፣ በዓመት ሦስት ጊዜ አምርቶ ለመጠቀም የሚያስችሉ ታላላቅ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የሕዝቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።
ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በአካባቢው ፈጣን ልማትና እድገት እንዲመጣ ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት እንደሚሠሩ የገለፁት ደግሞ አቶ ብርሃኑ ይርዳው ናቸው።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄ መሠረት ያደረገ ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ለሰው ተኮር ሥራዎች ቅድሚያ የሚሰጠው የመደመር መንግሥት በአካባቢው ከመንገድ፣ ከውሃ፣ ከመብራት፣ ከማኅበራዊና ከኢኮኖሚያዊ መስኮች ተጠቃሚነት አኳያ ከማኅበረሰቡ ለተነሱ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንደሚሰጥ አብራርተዋል።
በተጨማሪም የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታል በማድረግ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በመቀነስ የሕዝቡን እርካታ የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም፣ በክልሉ ለሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ስኬት ሕዝቡ ቅንጅታዊ ሥራውን ሊያጠናክር እንደሚገባም አሳስበዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።