በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የትምህርት መሠረተ ልማት ችግሮችን በመፍታት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤቶች ተደራሽነት እጥረትን ለመቅረፍ በአምስት ወራት ውስጥ በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ 42 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል የውል ስምምነት ከግንባታ ድርጅቶች ጋር ዛሬ ፈፅሟል።
በወቅቱም የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቡልቶሳ ሂርኮ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ትምህርት የትውልድን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመቅረጽና ሀገርን ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር መሠረታዊ ሚና አለው።
በመሆኑም በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ኃላፊው አያይዘውም በክልሉ የትምህርት መሠረተ ልማት ችግሮችን በመፍታት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ ብለዋል።
የ42ቱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታም ቢሮው የትምህርት መሠረተ ልማት እጥረትን በመቅረፍ ጥራት ያለው ትምህርት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከሚያከናውናቸው አበይት ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን አብራርተዋል።
ግንባታው በአምስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የተገለጸ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በክልሉ ያለውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እጥረት ለመቀነስ፣ የትምህርት ዕድልን ለማስፋትና ለተማሪዎች ምቹ የመማር ማስተማር ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ተማሪዎች በምቹ የመማሪያ ክፍሎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ከማድረጉም ባሻገር፣ የተማሪ-መማሪያ ክፍል ጥመርታውን የማሻሻል ሚና እንደሚኖረውም አስረድተዋል።
የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ በመንግሥት የግንባታ ድርጅቶች የሚከናወን ሲሆን፤ የተያዘለት የጊዜ ገደብና የጥራት ደረጃ ተጠብቆ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም ተገልጿል።