ቀጥታ፡

የጣና ፎረም የአህጉሪቱን ፈተናዎች በአፍሪካ መር መፍትሔዎች ለመፍታት አመላካች ውጤት አስገኝቷል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ የጣና ፎረም የአህጉሪቱን ፈተናዎች በአፍሪካ መር መፍትሔዎች ለመፍታት የሚያስችል አመላካች ውጤት ማስገኘቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አዳም ተስፋዬ ገለጹ።

የ12ኛው ጣና ፎረም ቅድመ ውይይት "የተለዋዋጭ ዓለምን በመቃኘት በአፍሪካ ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን የዲፕሎማሲና ውይይት ሚና" በሚል መሪ ሐሳብ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አዳም ተስፋዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት የጣና ፎረም ግልጽ፣ ገንቢ፣ አሳታፊና ነፃ የሐሳብ ውይይት የሚደረግበት መድረክ ነው።

ውቢቷ ባሕር ዳር በየዓመቱ የምታስተናግደው የጣና ፎረም፤ የአፍሪካ ሀገራት የአሁንና የቀድሞ መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የዘርፉ ባለሙያዎች በአህጉሪቱ በሚደቀኑ ፈተናዎች ዙሪያ ውይይት በማድረግ የፖሊሲ አማራጮችን የሚያቀርቡበት መድረክ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ የጸጥታና ደህንነት መዋቅር ፈጣን የጂኦፖለቲካ ለውጥና ኢ-ተገማችነት እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ አፍሪካ ይህንን ታሳቢ ያደረገ የራሷን መፍትሔ እንድትሰጥ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የጣና ፎረም ገንቢ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

የጣና ፎረም የአፍሪካ ችግሮችን በአፍሪካ መር መፍትሔዎች መፍታት እንደሚያስፈልግ አመላካች ውጤት የተገኘበት መሆኑንም አብራርተዋል።

እንደ ጣና ፎረም ባሉ መድረኮች የሚደረጉ ውይይቶች ለተቀናጀና ባለብዙ ወገን ትብብር፣ ለጋራ አረዳድ እንዲሁም የተጀመሩ የሰላም ጥረቶችን ለማጠናከር ወሳኝ መሆናቸውን አንስተዋል።

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ለጋራ ደህንነትና ሰላማዊ አብሮነት የሚበጁ ጥረቶችን እያደረገች መሆኑን ገልጸው፤ ሀገራዊና ቀጣናዊ ሁኔታዎችን በመቃኘት ለዘላቂ ሰላምና ደህንነት የሚሆኑ አማራጭ መንገዶችን ማሳየቷንም ተናግረዋል።

በፎረሙ ላይ የሚደረገው ውይይት ችግሮችን ከመመርመር ባሻገር መፍትሔዎችን ማፍለቅ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

ጣና ሐይቅ የዓባይ ወንዝ መነሻ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና ምሁራን ለዘላቂ ሰላምና ደህንነት አዳዲስ መንገዶችን የሚቀይሱበት ስፍራ መሆኑንም አንስተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የጣና ዳሯ ፈርጥ ባሕር ዳር የጣና ፎረምን በስኬት ስታካሂድ መቆየቷን ገልጸዋል።

ጣና ፎረም በቀጣናዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረግ የሚያስችል መድረክ ሆኖ መቀጠሉንም ተናግረዋል።

ፎረሙ ለአፍሪካውያን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ለመስጠት ፍቱን መድረክ መሆኑን ገልጸው፤ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የጋራ መግባባት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ በውይይት የተገኙ የመፍትሔ ሐሳቦችን በአሰራር በተደገፈ ተጨባጭ የተግባር እርምጃ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም