በሲዳማ ክልል የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር) ገለፁ።
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የ2019 በጀት ዓመት የክልሉን መንግሥት አስፈጻሚ አካላት የሥራ ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት በክልሉ የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በእርሻ ዘርፍ አርሶ አደሩ የምርታማነት ማሳደጊያ ፓኬጆችን በተሟላ መልኩ እንዲጠቀም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የምግብ ዋስትናና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ አስረድተዋል።
በተጨማሪም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን የማስፋት፣ የኤክስፖርት ምርቶችን የማሳደግና ገበያን የማረጋጋት ሥራ በትኩረት እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በእንስሳት ሀብት ልማት የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የዝርያ ማሻሻል፣ የእንስሳት ጤናና የመኖ አቅርቦትን የማሳደግ ሥራ በስፋት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራን ውጤታማ ለማድረግ የክህሎት ሥልጠና ከመስጠት ባለፈ የብድር፣ የመሥሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦትን የማሟላት ሥራ በቅንጅት እንደሚሠራም አብራርተዋል።
በውሃ፣ በጤና፣ በመንገድ፣ በትምህርትና በሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች ሕዝቡን የላቀ ተጠቃሚ ለማድረግ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ተጀምረው ያላለቁ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በተሻለ ፍጥነት አጠናቆ አገልግሎት የማስጀመር ተግባር እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የሕዝብ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የታገዙ፣ ቀልጣፋና የተገልጋይን እርካታ ያረጋገጡ እንዲሆኑ ተቋማትን የማጠናከር፣ በተለይም «መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በየአካባቢው የማስፋት ሥራዎች በትኩረት እንደሚከናወኑም ጠቅሰዋል።