ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት በማስከበር እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ክብር አለን - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት በማስከበር እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ክብር አለን
ወልደያ ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉዓላዊነት በማስከበር ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ክብርና ድጋፋችንን እንገልፃለን ሲሉ የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።
በሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙ የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች፤ ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት በማስከበር፣ ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ያላቸውን ክብርና ድጋፍ ገልጸዋል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል ወይዘሮ የትናየት አጋዡ፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገራዊ ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ያላቸውን አክብሮትና ድጋፍ ለመግለፅ በሕዝባዊ ድጋፍ ሰልፉ ላይ መገኘታቸውን ተናግረዋል።
አክለውም፣ ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ጠላቶች በመመከትና ዳር ድንበሯን በመጠበቅ እያከናወነ ያለው ተግባር አኩሪ በመሆኑ ከጎኑ በመቆም አጋርነታቸውን እንደሚያሳዩም ገልጸዋል።
የሕዝብና የሀገር ሰላምን ለማስቀጠል ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም አጋርነታችንን ማሳየት አለብን ያሉት ደግሞ ቀሲስ ሀብተማርያም ጸጋዬ ናቸው።
ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበርና ሰላምን ለማፅናት እየፈፀመው ላለው ወደር የለሽ ጀግንነት አክብሮትና ድጋፍ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ ያልጋ ጌታሁን በበኩላቸው፤ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰላምና የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል እየፈፀመ ላለው አኩሪ ተግባር ሕዝቡ ከጎኑ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
በድምቀት በተካሄደው ሕዝባዊ ትዕይንት ላይም ሕዝቡ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ያለው አጋርነት በግልጽ መታየቱንም አመልክተዋል።
በሰልፉ ላይ የተገኙት የሀገር ሽማግሌ አቶ ተገኘ አስፋው በበኩላቸው፤ ሠራዊቱ ለሰላምና ለሀገር ግንባታ እየከፈለ ለሚገኘው መስዋዕትነት ከፍተኛ አክብሮትና ድጋፍ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ለዚህም ኅብረተሰቡ ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ለሀገር ሰላም፣ ልማትና የጸና አንድነት ለማኖር እውነተኛ ደጀንነቱን እና ያለውን አጋርነት ሊያስጠብቅ እንደሚገባው በአጽንኦት ተናግረዋል።