ቀጥታ፡

ከተዘነጋ የኢኮኖሚ ክፍል ወደ ሀገራዊ ዕድገት ስትራቴጂካዊ ምሰሶነት፦ የማዕድን ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

አንድ ሀገር በተፈጥሮ ሀብት መባረኳ ብቻ ለብልጽግና አያበቃትም። ያለውን ሀብት አውቆ መለየት፣ በአግባቡ ማልማት፣ እሴት ጨምሮ ለሀገር ውስጥ ምርትና ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ራዕይና አቅም መገንባት ይጠይቃል። የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን የልማት አቅጣጫ ሲያስቀምጥ ከዚህ መሠረታዊ እውነታ በመነሳት በተፈጥሮ ሀብትና በሀገራዊ ብልጽግና መካከል ያለውን ርቀት ለማጥበብ ትኩረት ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ በከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ሀብቶች የታደለች ሀገር ብትሆንም፣ እነዚህን ሀብቶች ወደ ሀገራዊ ምርት፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢ፣ የሥራ ዕድልና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት የመቀየር አቅሟ ለረጅም ጊዜ በሚፈለገው ደረጃ አልተጠቀመችበትም። የማዕድን ዘርፉ እምቅ አቅምና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ሊኖረው የሚችለው ሚና ከሚፈለገው በታች ሆኖ ቆይቷል።

ይህንን እውነታ ለመቀየር የተፈጥሮ ሀብትን እንደ ተራ ጥሬ ዕቃ ሳይሆን እንደ የልማት ሞተር የሚመለከት አስተሳሰብ ያስፈልጋል። የመደመር መንግሥት በብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሪፎርም አማካኝነት ለማዕድን ዘርፉ የሰጠው ትኩረትም የዚህ ለውጥ አንዱ መገለጫ ነው። ሀብትን መለየት፣ ምርትን ማሳደግ፣ ኢንቨስትመንትን ማበረታታትና እሴት ጨምሮ የማቅረብ ስራን በማቀናጀት ዘርፉን ከተዘነጋ የኢኮኖሚ ክፍል ወደ ሀገራዊ ዕድገት ስትራቴጂካዊ ምሰሶነት ለመቀየር እየተሠራ ይገኛል።


 

ከራዕይ ወደ ተጨባጭ ውጤት-የአንድ የኢኮኖሚ ዘርፍ ለውጥ የሚለካው በታቀዱ ዕቅዶች ብቻ ሳይሆን፣ በሚፈጠረው ምርት፣ በሚያመነጨው ገቢና በሚፈጥረው የሥራ ዕድል ነው። በማዕድንና ከማዕድን ጋር በተያያዙ የኢንዱስትሪ ዘርፎች የታዩ እንቅስቃሴዎች የዚህን ለውጥ አቅጣጫ ያመለክታሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2018 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ብርጭቆ፣ ሴራሚክና ሌሎች ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል። በኢንዱስትሪ ዘርፉ ከታየው ፈጣን እድገት ጋር በተያያዘም የማዕድን ዘርፉ 24 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አመልክተዋል።

ይህ ውጤት የሚያሳየው የማዕድን ዘርፉ አስፈላጊነት በወርቅ ወይም በሌሎች ውድ ማዕድናት ሽያጭ ብቻ እንደማይገደብ ነው። ለግንባታ፣ ለማምረቻ፣ ለኃይልና ለግብርና የሚውሉ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማቅረብ ከተቻለ፣ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ከመቀነስ ባለፈ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እንዲጠናከሩ ያስችላል።

ወርቅ፦ ከጥሬ ማዕድን ወደ ከፍተኛ ሀገራዊ እሴት-ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ዘርፎች መካከል የወርቅ ዘርፍ የሚጠቀስ ነው። በተለይም በ2018 ዓ.ም. ከወርቅ ወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 5.7 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ለዚህ አብነት ነው። ይህ አፈጻጸም የወርቅ ሀብትን በተሻለ ሁኔታ ወደ ሀገራዊ ገቢ የመቀየር አቅም እየጎለበተ መምጣቱን ያሳያል።

ነገር ግን የወርቅ ሀብትን በጥሬው መሸጥ ብቻ በቂ አይደለም። ለዚህም የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ መመረቅ በዘርፉ የታየ ጠቃሚ እርምጃ ነው።

ፋብሪካው በመጀመሪያው ምዕራፍ በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማጣራት አቅም ያለው ነው። ይህ አቅም በሀገር ውስጥ የማጣራት አገልግሎትን ከማጠናከር ባለፈ፣ ከምሥራቅ አፍሪካና ከሌሎች አካባቢዎች የማዕድን አቅርቦት ለመሳብ ዕድል ሊፈጥር ይችላል።

ዋናው ፋይዳ ግን በማጣራት ብቻ አያበቃም። የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ማስፋፋት፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠርና ከማዕድን የሚገኘውን እሴት በሀገር ውስጥ ለማሳካት መሠረት ይጥላል።

የማዕድን እሴት ጭማሪ፦ የኢንዱስትሪ ልማት መሠረት- የማዕድን ሀብት የኢኮኖሚ ፋይዳ የሚጎለብተው ጥሬ ዕቃን ወደ ዝግጁ ምርት በሚቀይርበት ሂደት ነው። በዚህ ረገድ የድንጋይ ከሰልን፣ ለጌጣጌጥ የሚውሉ ማዕድናትንና ሌሎች የተፈጥሮ ግብዓቶችን በማቀነባበር ለገበያ ማቅረብ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል።

የሴራሚክ ምርትም በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ምሳሌ ነው። ከዚህ ቀደም ከውጭ በስፋት ይገባ የነበረውን ምርት በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉ፣ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለመሸፈንና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ዕድል ይፈጥራል። በተመሳሳይ የማዕድን ሀብቶችን ለጌጣጌጥ ምርት ማዋል ከጥሬ ማዕድን ሽያጭ የበለጠ እሴት ለመፍጠር ያስችላል።


 

ይህ ሂደት አምራቾችን፣ ነጋዴዎችንና በተለያዩ የአቅርቦት ሰንሰለቶች ውስጥ የሚሳተፉ ዜጎችን በማገናኘት ሰፊ የኢኮኖሚ ትስስር ይፈጥራል። ስለዚህ የማዕድን ሀብትን በሀገር ውስጥ ማቀነባበር የኢንዱስትሪ ልማትን ከማፋጠን ባለፈ የዜጎችን ተሳትፎ የሚያሳድግ የልማት መንገድ ነው።

የድንጋይ ከሰል፦ ለሲሚንቶ ኢንዱስትሪ የሀገር ውስጥ ግብዓት- ኢትዮጵያ ያላትን የድንጋይ ከሰል ሀብት በኢንዱስትሪ ውስጥ ለመጠቀም ያላት አቅም የሚታይበት ዘርፍ የሲሚንቶ ምርት ነው። ቀደም ሲል የሀገሪቱ ድንጋይ ከሰል ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት በተሟላ ሁኔታ ሊውል አይችልም የሚል አመለካከት እንደነበር ቢገለጽም፣ በተደረጉ ምርምሮችና በተግባር በተገኙ ማሳያዎች ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ግብዓት ሊሆን እንደሚችል ታይቷል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የድንጋይ ከሰል ምርት እድገት ማሳየቱና በአሁኑ ወቅት የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ለማሟላት መቻሉ በዘርፉ የታየ ተጨባጭ ለውጥ ነው። 

የሲሚንቶ ምርትም በ2014 ዓ.ም. ከነበረው 6.2 ሚሊዮን ቶን በ2018 ዓ.ም. ወደ 10.4 ሚሊዮን ቶን አድጓል። የሀገሪቱ የማምረት አቅም 17 ሚሊዮን ቶን እንደሚደርስም መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም ለግንባታ ዘርፉ የሚያስፈልገውን ግብዓት ለማቅረብና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት የበለጠ ዕድል ይፈጥራል።

የተፈጥሮ ጋዝና የጂኦተርማል ኃይል፦ የወደፊት ኢኮኖሚ አቅም- የማዕድን ሀብት ፋይዳ በጠንካራ ማዕድናት ብቻ አይወሰንም። የተፈጥሮ ጋዝና የጂኦተርማል ኃይል ሀብቶችም ለኢትዮጵያ የወደፊት የኢኮኖሚ ለውጥ ወሳኝ አቅሞች ናቸው።

የተፈጥሮ ጋዝ ምርትን ማሳደግ ከውጭ የሚገባውን የነዳጅና የኃይል ግብዓት ጥገኝነት ለመቀነስ ዕድል ይፈጥራል። በተጨማሪም ጋዝን ለዩሪያ ማዳበሪያ ምርት እንደ ግብዓት መጠቀም ከተቻለ፣ ለግብርና ምርታማነትና ለኢንዱስትሪ ዕድገት ጠቃሚ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

በተመሳሳይ፣ የጂኦተርማል ኃይልን ማልማት የኃይል ምንጮችን ለማብዛትና ለኢንዱስትሪዎች የተረጋጋ የኃይል አቅርቦት ለማረጋገጥ ያግዛል። እነዚህን ሀብቶች በዕውቀት፣ በቴክኖሎጂና በተገቢ ኢንቨስትመንት ማልማት ከተቻለ፣ የሀገሪቱን የኃይል ደኅንነት ከማጠናከር ባለፈ አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን ይከፍታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም