የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገራችን ኩራትና የክብራችን መገለጫ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገራችን ኩራትና የክብራችን መገለጫ ነው
ገንዳ ውሃ ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገራችን ኩራትና የክብራችን መገለጫ በመሆኑ ልንደግፈውና ልናመሰግነው ወጥተናል ሲሉ በገንዳ ውሃ ከተማ ለድጋፍ ሰልፍ የወጡ ተሳታፊዎች ገለጹ።
በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተለያዩ መልዕክቶች የተላለፉበት የሀገር መከላከያን የሚደግፍ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰልፉ ታዳሚዎች፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ብዙ አሲረው የተለያዩ የጥፋት ሙከራዎችን ቢያደርጉም በሰራዊታችን ጀግንነት እየተመከቱ መሆኑን ገልጸዋል።
የውስጥ ባንዳዎች የጥፋት ተልእኮ ተቀብለው ሀገር ለማተራመስ ያደረጉት ጥረትም በሰራዊታችን ብርቱ ክንድ መክኗል ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም ይህንን የሀገር ባለውለታና የህዝብ አለኝታ የሆነ ሰራዊት መደገፍ፣ ማገዝና ማመስገን ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል መምህር ዳኘው አዲስ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የላቀ ምስጋና እና ተገቢው ክብር ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ወይዘሮ ስንታየሁ ሲሳይ እና መሪጌታ አዱኛ መለሰ፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገራችን ኩራትና የክብራችን መገለጫ በመሆኑ ልንደግፈውና ልናመሰግነው ወጥተናል ሲሉ ተናግረዋል።
በምእራብ ጎንደር ዞን በገንዳ ውሃ ከተማ በተካሄደው የህዝባዊ ድጋፍ ሰልፍ የሃይማኖት አባቶች፣የሃገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
ከማለዳ ጀምሮ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የሚደግፍ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች መካሄዱ ይታወቃል።