ቀጥታ፡

የትግራይ ክልል የባለአደራ አስተዳደር ህዝባዊ አገልግሎቶችን የማነቃቃት ተግባርን በቀዳሚነት እንወጣለን - ከንቲባ ሽሻይ አማረ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ የትግራይ ክልል የባለአደራ አስተዳደር ህዝባዊ አገልግሎቶችን የማነቃቃት ተግባርን በቀዳሚነት እንወጣለን ሲሉ የመቐለ ከንቲባ ሆነው የተሾሙት ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) ገለፁ።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 14/2/ለ/ መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ባስተላለፈው ውሳኔ እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ የኢፌዴሪ መንግሥት የትግራይ ክልልን የሚያጸና ውሳኔ ወስኗል።

በዚህም የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ትግራይን የሚያስተዳድር ይሆናል።

የባለአደራ አስተዳደሩ በሚያከናውናቸው ሁሉም ተግባራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት፣ የትግራይ ሕዝብን መሠረታዊ ጥቅሞች መሠረት ማድረግ ይጠበቅበታል።

በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስከሚቋቋም ድረስ የክልሉን የዕለት ተዕለት አገልግሎቶች ከማቅረብና ለቀጣይ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎችን ከመፍጠር በዘለለ ረዘም ያለ ስትራቴጂያዊ አንድምታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ እንደማይንቀሳቀስም ተገልጿል።

ባለአደራ አስተዳደሩም ተግባሩን ከፌዴራል መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ እና መመሪያ መሠረት ያከናውናል።

በባለአደራው አስተዳደር የመቐለ ከንቲባ ሆነው የተሾሙት ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የህገ ወጡ ህወሃት ቡድን የጥፋት እና የቁማር ፖለቲካ ለመጨረሻ ጊዜ አብቅቷል።

የተቋቋመው ባለአደራ አስተዳደር ዋና እና ቀዳሚ ተግባሩ ሰላምና መረጋጋት በማስፈን መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎቶችና መሰረተ ልማት ስራዎችን ማጠናከር መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን ተግባር በብቃት ለመወጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ቀዬያቸው መመለስ እና ኢኮኖሚን ማነቃቃትም በባለአደራ አስተዳደሩ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው ብለዋል።

የትግራይ ክልል ህዝብ ዴሞክራሲ ስርዓት፣ እኩልነት እና ፍትህን ለማረጋገጥ ለረጅም ጊዜ ዋጋ ከፍሏል ያሉት ዶክተር ሽሻይ፤ በቀጣይም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና ህዝቡ በመረጠው መንግስት እንዲተዳደር ለማድረግ የሚያስችሉ አዳዲስ ህጎች ፣ አሰራሮች እና ውሳኔዎች በማውጣት ሃላፊነታቸውን በሚገባ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ለቀጣይ ምርጫ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ትኩረት እንደሚሰጠውም ተናግረዋል።

የፌዴራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር ተልዕኮውን ለመፈፀም ከህዝቡ ከሲቪክ ማህበራትና ከሚመለከታቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመተባበር እንደሚሰሩም ዶክተር ሽሻይ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም