ቀጥታ፡

በክልሉ ያለውን እምቅ ሃብትና የህዝቡን የተደመረ አቅም በመጠቀም ለእድገትና ማንሰራራት መትጋት ይጠበቅብናል

ወራቤ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ በክልሉ ያለውን እምቅ ሃብትና የህዝቡን የተደመረ አቅም በመጠቀም ለእድገትና ማንሰራራት መትጋት ይጠበቅብናል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለጹ።

የመደመር መንግስት የህብረተሰብ አቀፍ የምክክር መድረክ በወራቤ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


 

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)፤  በክልሉ ያለውን እምቅ ሃብትና የህዝቡን የተደመረ አቅም በመጠቀም ለእድገትና ማንሰራራት መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመለየትና በዘላቂነት በመፍታት በጋራ ማልማት ያስፈልጋልም ብለዋል።

ለዚህም የአመራሩ ቁርጠኝነትና የመፈፀም ዝግጁነት መኖሩን አረጋግጠው የህዝቡም ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።


 

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ፤ በዞኑ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናቆ ለአገልግሎት ማዋልና ሌሎች የልማት ስራዎችንም አጠናክሮ የመቀጠል ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

በመሆኑም የመደመር መንግስትን ጥልቅ እሳቤና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማገዝ ለዘላቂ ልማት የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)፤ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የመደመር መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም የመንግስትን ጥረትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመደገፍ ህዝቡ ለጋራ ስኬትና ተጠቃሚነት የጀመረውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም