ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር የሁሉም ተሳትፎ ያስፈልጋል - አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር የሁሉም ተሳትፎ ያስፈልጋል ሲሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ( ዶ/ር) ገለጹ።

የዓባይና ቀይ ባህር ስትራቴጂክ ፎረም ያዘጋጀው እና "ዓባይ፣ ቀይ ባህርና የጋራ ተጠቃሚነት" በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ( ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ዓባይና ቀይ ባህር የማይነጣጠሉ ናቸው። 


 

ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ታሪካዊም ተፈጥሯዊ  መነሻ እንዳላት ጠቅሰው፤  በቀይ ባህር በኩል ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስታካሂድ መቆየቷን አንስተዋል።  

በቀይ ባህር ላይ ከጥንት ጀምር ወደቦችን አልምታ ስትጠቀም መቆየቷን አስታውሰው፤ ከአገሮች ጋርም የነበራትን ኢኮኖሚያዊ ትብብሮችንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

ቀይ ባህር የኢትዮጵያ የፀጥታ ዋስትና ሆኖ ለዘመናት ዘልቋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህም ታሪክ የሚያስረዳው እውነት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሴራ ከቀይ ባህር  እንድትርቅ መደረጉን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም መከበር የሁላችንም ተሳትፎ እንደሚፈልግ ተናግረዋል። 

ለዚህ ደግሞ የጋራ ግንዛቤ መያዝ ወሳኝ ነው ያሉት አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ፎረሙ ያዘጋጀው ውይይት ወቅታዊ እና ጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል።


 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደህንነት መምህርና ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በቀጣናው ሁሉንም አሸናፊ ለማድረግ ከውድድር ይልቅ ትብብርን ማስቀደም ወሳኝ ነው ብለዋል።    

የአፍሪካ ቀንድ ህልውና የሚወሰነው የውሃ ኃብቶቹን ሁሉም ወገኖች የሚጠቀሙበት ፍትሃዊ፣ ሕጋዊና ዘላቂ ሥርዓት በመዘርጋት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

በውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት የስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ዳይሬክተርና ከፍተኛ ተመራማሪ ጋሻው አይፈራም (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ  ከፉክክር ወደ ትብብር የሚያመጣ ፖሊሲ እየተከተለች መሆኑን አንስተዋል።   


 

በአንጻሩ ግብጽ "እኛ" ከማለት ይልቅ "እኔ የሚል መንገድ መምረጧን ገልጸው፤ ይህ ደግሞ ከመርህ አኳያም ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው ብለዋል።    

ኢትዮጵያ በቀጣናው የምታራምደው የትብብር ፖሊሲም በጥሩ መስመር ላይ እንድትጓዝ ማስቻሉን አመልክተው፤ ይሄንን ይበልጥ አጠናክሮ መጠቀል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በታላቁ ህዳሴ ግድብ የተገኙ ድሎች ተሞክሮ በመቀመር ቀጣናዊ ትስስሮችን ማስኬድ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።


 

በውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት የማሪታይም ዲፕሎማሲ ተመራማሪ ሽመልስ ኃይሉ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር መመለስ ለቀጣናው ሠላምና መረጋጋት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው።  

ለቀጣናው ንግድ መሳለጥ የኢትዮጵያ ወደ ባህር በር መመለስ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕግጋቶች እና መርህን የተከተለ እና ተገቢ መሆኑን የሚያጎሉ ሥራዎች በይበልጥ መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም