ቀጥታ፡

በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 28 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል

ጅማ ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 28 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) ገለጹ።

በዞኑ ሊሙ ኮሳ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተከናውኗል። 

መርሃ ግብሩን በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ ረሻድ ከማል (ዶ/ር)ን ጨምሮ የተለያዩ የዞን እና የወረዳ የሥራ አመራሮች ተገኝተው አስጀምረዋል።


 

በወቅቱም የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ እንደተናገሩት፤ በመንግሥት ደረጃ የተያዘውን አቅጣጫ ይበልጥ ተግባራዊ ለማድረግ በዞኑ ለተለያዩ የግብርና ኢኒሼቲቮች ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።

በዘንድሮው ዓመት በዞኑ ከ700 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰው፣ ከዚህም 28 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። 

ለአርሶ አደሩ አስፈላጊ የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ፣ ሙያዊ እገዛና ክትትል በማድረግ የታቀደውን ውጤት ለማሳካት በትኩረት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።


 

የሊሙ ኮሳ ወረዳ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በስንዴ ልማት ስኬታማ የግብርና ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ቀደም ብሎ በመንግሥት በኩል አስፈላጊ የግብርና ግብዓቶች በመቅረባቸው በዘንድሮው ምርት ዘመን የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም