ሠራዊቱ ሰላምን በማስጠበቅ የሀገርን ልማት ለማስቀጠል እየፈፀመ ላለው ጀብዱ ታላቅ ክብር ይገባዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ ሰላምን በማስጠበቅ የሀገርን ልማት ለማስቀጠል እየፈፀመ ላለው ጀብዱ ታላቅ ክብር ይገባዋል
ጎንደር ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦የሃገር መከላከያ ሰራዊት ሰላምን በማስጠበቅ የሀገርን ልማት ለማስቀጠል እየፈፀመ ላለው ጀብዱ ታላቅ ክብር ይገባዋል ሲሉ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ።
በጎንደር ከተማ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍና የጥፋት ኃይሎችን የሚያወግዝ ሕዝባዊ የድጋፍ ትዕይንት ዛሬ ተካሄዷል።
በሕዝባዊ የድጋፍ ትዕይንቱ ላይ በመገኘት የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እንደገለጹት፤ ሠራዊቱ የሕዝብን ሰላምና የሀገርን ልማት የማስቀጠል ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ ይገኛል።
ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነትና የሕዝብን ዘላቂ ሰላም ለማስከበር እየፈፀመ ላለው ጀብዱ ታላቅ ክብር ይገባዋል ብለዋል።
በበረሃና በቁሩ፣ በዳገትና በቁልቁለቱ ፍጹም መስዋዕትነት እየከፈለ የሕዝብን ሰላምና የሀገርን ልማት በማስቀጠል ረገድ የላቀ ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የጎንደር ሕዝብም ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሁሉ አሁንም ሆነ ወደፊት ለሠራዊቱ የማይበገር የብረት ደጀንና የታመነ ረዳት ሆኖ እንደሚቀጥል ቁርጠኝነቱን አሳይቷል ብለዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ፍትሐዊ ጥያቄ በሰጥቶ መቀበል መርህ እና በልጆቿ ጽናት እውን የሚሆን ሀገራዊ ራዕይና ትውልዳዊ ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል።
ሠራዊቱ የህዝብን ሰላምና ልማት ለማቀጠል በቁርጠኝነት እየተጋ መሆኑን የገለፁት በህዝባዊ ድጋፉ ላይ ያገኘናቸው አቶ አምባቸው በላይ፤ ሕዝቡም ከጎኑ በመሰለፍ አስፈላጊውን ድጋፍና አጋርነት እንደሚያሳይ አረጋግጠዋል።
ቤተልሔም ደጉ በበኩሏ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነት ዋስትናና የሕዝብ ደጀን በመሆኑ በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ከጎኑ መሆኗን ገልጻለች።
በጎንደር ከተማ በተካሄደው የመከላከያ ሠራዊት ህዝባዊ የድጋፍ ትዕይንት ላይ የከተማውና የዞኑ አስተዳደር አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና በርካታ ነዋሪዎች በመገኘት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ጽኑ ድጋፍ ገልጸዋል።