ቀጥታ፡

በግብርና ምርምር የተገኙ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች ምርትና ምርታማነትን እያሳደጉ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦የግብርና ምርምር ስራዎችን ከመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ጋር በማቀናጀት በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች ምርትና ምርታማነትን  ማሳደጋቸውን በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

የግብርና ዘርፉን ለማዘመንና ለማሸጋገር በምርምር የተገኙ ውጤቶችና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ በጥራትና ፍጥነት ተደራሽ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የመደመር መንግሥት የግብርና ዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በወሰዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች በምርት እና ምርታማነት ላይ ውጤቶች መመዝገባቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።


 

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ፈቃዱ ጉርሙ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በምርምር የሚገኙ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች ለምርትና ምርታማነት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።

ሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥና የአርሶ አደሩን ገቢ ማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ ዝርያዎችን፣ የሰብል እንክብካቤና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ድርቅን የሚቋቋሙ ዝርያዎች፣ በየጊዜው ከሚከሰቱ የሰብል በሽታዎችና ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ጋር የሚላመዱ፣ በአነስተኛ የዝናብ እርጥበት ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎች እየቀረቡ መሆኑንም ገልጸዋል።

አርሶ አደሮች አዳዲሶቹን የምርምር ውጤቶችና ቴክኖሎጂዎች በመጠቀማቸው በሔክታር የሚያገኙት ምርት በእጥፍ እያደገ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የምርምር ውጤቶች በስፋት ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ ከተለያዩ የልማት አጋሮችና ከግብርና ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በቀጣይም ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቷን የግብርና ክፍለ-ኢኮኖሚ ለማዘመንና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ፣ የገበያ ፍላጎትን ያገናዘቡና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ አዳዲስ የግብርና አሰራሮችንና ዝርያዎችን የማላመድ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

አርሶ አደሩ ከምርምር ማዕከላት የሚወጡ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና ዝርያዎችን እንዲሁም የሚቀርቡ ሙያዊ ምክሮችን በአግባቡ በመተግበር ምርታማነቱን የበለጠ እንዲያሳድግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከኢንስቲትዩቱ የሚወጡ አዳዲስ የምርምር ውጤቶች በስፋት ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ የሙያተኞችና የስራ ኃላፊዎች ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም