ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ቀዳሚ የአቪዬሽን ማዕከል ለመሆን የሚያስችለውን ተግባር እያከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ቀዳሚ የአቪዬሽን ማዕከል ለመሆን የሚያስችለውን ተግባር እያከናወነ መሆኑን ዓለም አቀፉ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ኤርባስ ገለጸ።  

በቀጣዮቹ 20 ዓመታት የኢትዮጵያ የአየር መንገደኞች ቁጥር ስድስት እጥፍ ያድጋል ሲልም ተንብዮአል።

የኤርባስ የገበያ ትንተናና ትንበያ ምክትል ፕሬዚዳንት አንቶኒዮ ዳ ኮስታ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ከፍተኛ የዕድገት አቅም ያላት ሀገር ናት።

አየር መንገዱም እያደገ የመጣውን የተሳፋሪ ፍላጎት፣ እየጨመረ የሚሄደውን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትስስር ለማጠናከር የሚያስችል አቅም እየገነባ ይገኛል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጋር በመሆናችን እጅግ ኩራት ይሰማናል ያሉት ዳ ኮስታ፤ አየር መንገዱ በአፍሪካ የመጀመሪያው የኤ350 ደንበኛ በመሆን ላለፉት 10 ዓመታት ከኩባንያቸው ጋር በትብብር ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

የአየር መንገዱ ጠንካራ የበረራ አውታርና አቅም ያለው መሆን በቀጣይ እያደገ የሚመጣውን የተሳፋሪዎች ቁጥር ለማስተናገድ የሚያስችል ስትራቴጂክ ማዕከል ያደርገዋል ብለዋል።

በቀጣዮቹ 20 ዓመታት የተሳፋሪዎች ቁጥር በስድስት እጥፍ ማደግ የሚያስችል የዕድገት አቅም እንዳለው መተንበዩን አንስተው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን ለማስተናገድ የሚያስችል አቅም እንዳለው ገልጸዋል።

የአፍሪካ የአየር ትራፊክ ሦስት እጥፍ እንደሚያድግ መተንበዩንና ይህም አየር መንገዶችና አየር ማረፊያዎች አቅም ለማጎልበትና በአህጉሪቱና ከአህጉሪቱ ባሻገር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።


 

እየተገነባ የሚገኘው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ የታቀዱ የአየር ማረፊያ መሠረተ ልማቶች ሀገሪቱ በአፍሪካ አቪዬሽን ውስጥ ያላትን ሚና የሚያጎሉ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላለፉት ዓመታት በአቪዬሽን ዘርፉ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ታሪካዊ የአፍሪካ አየር መንገድ መሆኑን አንስተዋል።

ኤርባስ ዘመናዊ አውሮፕላኖችንና አሰራሮችን በማቅረብ ብሎም ቴክኒካዊ ድጋፍ በማድረግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በትብብር መሥራቱን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የመንገደኞች ዕድገት የኢትዮጵያን የአፍሪካ አቪዬሽን ዋነኛ መተላለፊያ መስመር መሆን የሚያጠናክር ሲሆን የመሠረተ ልማት ማስፋፊያዎቹም ለአየር መንገዱ እድገት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም