በሐረሪ ክልል የሚከናወኑ የተለያዩ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል የሚከናወኑ የተለያዩ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተደረገ ነው
ሀረር፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል የሚከናወኑ የተለያዩ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እንዲሁም ሌሎች የካቢኔ አባለት፤ በሀረር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የወንዝ ዳር ፕሮጀክት፣ የተቋማት ማዕከል፣ የመንገድና የኮሪደር ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ከጉብኝቱ በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ የፕሮጀክቶቹ የግንባታ ሂደት በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማት፣ የመንገድና ሌሎችም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው በዚሁ መሰረት ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የተለያዩ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ በተደመረ አቅም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ የመሰረተ ልማት ተደራሽነትን ከማሳደግ ባሻገር የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ በማሻሻል በብዙ መልኩ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አንስተው ለስኬቱ የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የኮሪደር ልማቱ በሀረር ከተማ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣቱን የገለጹት ርእሰ መስተዳድሩ በቀጣይነትም ተያያዥ የልማት ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።