በመንግሥት የተፈጠረልን የሥራ ዕድል ሠርተን እንድንለወጥ አስችሎናል - ኢዜአ አማርኛ
በመንግሥት የተፈጠረልን የሥራ ዕድል ሠርተን እንድንለወጥ አስችሎናል
ዲላ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦በዲላ ከተማ በማኅበር ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡ ወጣቶች በመንግሥት በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ሠርተው በመለወጥ ራሳቸውን እንደቻሉ ተናገሩ።
በከተማው የ"ኤልሻዳይ የዳቦ አቅራቢ ማህበር" አባል ወጣት ሰናይት ብርሃኑ፤ ከከተማ አስተዳደሩ በተደረገላቸው የብድር፣ የመስሪያ ማሽን እና የመሸጫ ሼድ ድጋፍ እሷን ጨምሮ አምስት ወጣቶች ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግራለች።
በአሁኑ ወቅት በተለያየ መጠን በቀን እስከ 3 ሺህ ዳቦ ጋግረው ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን የገለጸችው ወጣት ሰናይት፤ የተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ራሳቸውን ለመቻልና ለመለወጥ ያላቸውን ራዕይ ለማሳካት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጻለች።
ባገኙት የክህሎት ስልጠናና የቴክኖሎጂ እገዛ ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን የገለጸው ደግሞ የ"አቢ የቤትና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ማህበር" ሰብሳቢ ወጣት ፀጋአብ አስናቀ ነው።
ሥራ በጀመሩ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ በርካታ ትዕዛዞችን ተቀብለው የተለያዩ የቤትና የቢሮ እቃዎችን በማምረት ለተጠቃሚዎች ማቅረባቸውን ተናግሯል።
በአሁኑ ወቅት ከማህበሩ አባላት በተጨማሪ ለሦስት ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም አክሏል።
የ"ኪቾ ምግብ ዝግጅት ማህበር" አባል ወጣት ሀብታሙ አየለ በበኩሉ፤ ባገኙት 150 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል በምግብ ዝግጅት ሥራ መጀመራቸውን ገልጿል።
ይህም ከሥራ አጥነት ተላቀው ራሳቸውን ለመቻል የሚያደርጉትን ጥረት ማገዙን ጠቅሶ፣ ሥራቸውን አጠናክረው ለመቀጠል የማምረቻ ቦታ (ሼድ) እንዲመቻችላቸው ለመንግስት ጥያቄ አቅርበው እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግሯል።
የዲላ ከተማ ምክትል ከንቲባና የሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታሪኩ በየነ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ የአካባቢውን ጸጋዎች በመጠቀም ከ4 ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚሁ መሠረት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 661 ዜጎችን ወደ ሥራ ለማስገባት መቻሉን ገልጸው፣ ወደ ሥራ የገቡትም ውጤታማ እንዲሆኑ በክህሎት የማብቃት ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።
የሥራ ዕድሉ የተፈጠረው በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎት እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታሪኩ፤ አፈጻጸሙን ለማሻሻል በክህሎት መር ስልጠና፣ በሼድ እና የመሬት አቅርቦት ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ለውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ፈጠራም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።