ኢትዮጵያ ለ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከዩጋንዳ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ታደርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከዩጋንዳ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ታደርጋለች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ከዩጋንዳ አቻው ጋር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከቀኑ 7 ሰዓት ከ30 ላይ በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ይካሄዳል።
በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምድብ ሁለት አራት ነጥብ በመሰብሰብ በምርጥ ሁለተኝነት ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፏል።
የተጋጣሚው የዩጋንዳ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምድብ አንድ በአራት ነጥብ አንደኛ ሆኖ በማጠናቀቅ አራት ውስጥ ገብቷል።
ሁለቱ ቡድኖች በምድቡ እርስ በእርስ ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው ይታወቃል።
ዘሚካኤል ምንያህል ለኢትዮጵያ፣ አርኖልድ ካዬምባ ለዩጋንዳ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ 2026 በሞሮኮ በተካሄደው 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳትፎ አድርጋለች።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ካሸነፈ ለፍጻሜ ከማለፍ ባሻገር የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎውን ያረጋግጣል።
ብሔራዊ ቡድኑ ቢሸነፍም በደረጃው ጨዋታ ድል ቀናው ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ሁለተኛ እድል አለው።
በሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር ሩዋንዳ ከሶማሊያ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በውድድሩ ላይ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የሚወጡ ሀገራት የሴካፋ ዞንን ወክለው እ.አ.አ በ2027 በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 17ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መረጃ ያመለክታል።
በሞሮኮ አስተናጋጅነነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ራሷን ሞሮኮን ጨምሮ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።