የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና 53ኛው የፕሪሚየር ሊግ የደርቢ ጨዋታ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና 53ኛው የፕሪሚየር ሊግ የደርቢ ጨዋታ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7 /2019 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በመክፈቻው ጨዋታ ከነገሌ አርሲ ጋር አንድ አቻ ተለያይቷል። ቡድኑ በአንድ ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በሸገር ከተማ የ1 ለ 0 ሽንፈት ያስተናገደ ሲሆን ያለ ምንም ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቡድኖቹ በሊጉ እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለ53ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም 51 ጊዜ ተጫውተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 22 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ኢትዮጵያ ቡና 10 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 20 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
በ52ቱ ጨዋታዎች በድምሩ 102 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 65 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 37 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
በ2018 ዓ.ም ባደረጓቸው የሊግ ጨዋታዎች በተመሳሳይ አንድ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል።
ኢትዮጵያ ቡና የሊጉን ዋንጫ አንድ ጊዜ ያነሳ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 16 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።
የዛሬው ጨዋታ ሁለቱ ክለቦች የመጀመሪያ የሊግ ድላቸውን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ነው።
የሁለቱ ክለቦች በርካታ ደጋፊዎች ለጨዋታው ድምቀት ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሃዋሳ ከተማ በመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታው በመቻል የ1 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል።
ኢትዮጵያ መድን አዲስ አዳጊውን ጋሞ ጨንቻን 2 ለ 0 ረትቷል።
ጨዋታው ሃዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት፣ ኢትዮጵያ መድን በድል ጉዞው ለመቀጠል የሚያደርጉት ነው።
ጋሞ ጨንቻ ከሲዳማ ቡና ዛሬ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ሲዳማ ቡና ከሱዳኑ አል ሂላል ኦምዱርማን ጋር በሚያከናውነው የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል።