የመጀመሪያው የአፍሪካ ወታደራዊ ማርቺንግ ባንዶች ውድድርና ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመጀመሪያው የአፍሪካ ወታደራዊ ማርቺንግ ባንዶች ውድድርና ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦የመጀመሪያው የአፍሪካ ወታደራዊ ማርቺንግ ባንዶች ውድድርና ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ ከሁሉም የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የተውጣጡ ማርቺንግ ባንዶች የሚሳተፉ ሲሆን አህጉራዊ አብሮነት የሚጠናከርበት እና ትዕይንቶች የሚቀርቡበት መሆኑ ተመላክቷል።
መርሀ ግብሩን የመከላከያ ሚኒስቴር፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን ከታህሳስ 2 እስከ 5 ቀን 2019 ዓ .ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
መርሀ ግብሩን አስመልክቶ የመከላከያ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ማብሰሪያ እና መርሃ ግብሩን ለማካሄድ በተደረጉ ዝግጅቶች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጫ መርሃ ግብር ተካሄዷል።
በመርሐግብሩ ላይ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች፣ዲፕሎማቶች የቀድሞ ሰራዊት አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ሮዛ የሩቅነህ እንዳሉት፤ መርሃ ግብሩ ሀገራት ያላቸውን ትብብር እንዲያጠናክሩ አዎንታዊ ሚና አለው።
ውድድርና ፌስቲቫሉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በሁሉም መስክ የሚያሳልጥ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ200 በላይ ስብሰባዎች ማስተናገዷን አስታውሰው፤ ይህንንም መርሃ ግብር በብቃት ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ለመርሃ ግብሩ ስኬት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ በማብሰሪያ መርሃ ግብር ላይ እየተሳተፋ ያሉ ወታደራዊ አታሼዎች ውድድሩና ፌስቲቫሉ ዓላማውን እንዲያሳካ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የውድድሩ እና ፌስቲቫሉ ሃሳብ አመንጪ እና የቀድሞ መከላከያ ሰራዊት አባል ሻለቃ ቆንሲል ተስፋዬ ወንድሙ፤ የመርሀ ግብሩ ዓላማ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም መርሀ ግብሩ ወታደራዊ ማርቺንግ ባንዶች ትውፊታቸውን እና ባህላቸውን የሚያስተዋውቁበት ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቁመዋል።
አፍሪካዊ ትብብርን ማጠናከር ዙሪያም በጋራ ለመስራት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አክለዋል።
ውድድሩ የጎዳና ላይ ሰልፍ ፣የሜዳ ላይ ትርኢት፣የልዩ ሙዚቃዎች ውድድርን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።