ቀጥታ፡

ግብፅ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገትና እያደገ የመጣ ቀጣናዊ ተፅዕኖ እንደ ስትራቴጂክ ተግዳሮት ትመለከታለች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦ግብፅ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳታገኝ የምታደርገው ተቃውሞ፣ የሀገሪቷን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለመገደብና እያደገ የመጣውን የቀጣናዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ሚና ለማዳከም የተዘጋጀ የስትራቴጂ አካል መሆኑን ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊ የፖለቲካ ሳይንቲስትና ጠበቃ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም ገለጹ።

በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሳን በርናርዲኖ ያስተማሩት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማረያም ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ግብፅ በኢትዮጵያና በዓባይ ተፋሰስ ላይ ያላት ፍላጎት ከ1820ዎቹ ዓመታት ጀምሮ ነው። 

በወቅቱ ግብፅ በዓባይ ላይ ቁጥጥሯን ለማስፋት በማሰብ በሱዳን በኩል ወታደሮችን ልካ እንደነበር አስታውሰው፤ ሆኖም በወቅቱ ጥረቷ እንዳልተሳካ ገልጸዋል።

ግብፅ በመቀጠል በ1875 እና 1876 በኢትዮጵያ ላይ ታላላቅ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ከፍታ እንደነበር አውስተው፤ ዘመቻዎቹ በጉንደትና በጉራ ጦርነቶች በሽንፈት መጠናቀቃቸውን አንስተዋል።

ይህም የግብፅን በኢትዮጵያ ወታደራዊ የበላይነት ለማግኘት የነበረ ፍላጎት ያከሸፈ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የግብጽ ስትራቴጂካዊ ፍላጎት በዓባይ ውሃን በበላይነት የመቆጣጠር ላይ ማተኮሩንና የግብፅ መሪዎች ዓባይን የራሳቸው መብት አድርገው እንደሚቆጥሩት ተናግረዋል።

የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችና ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች የግብፅን አቋም የሚያጠናክሩ ቢሆኑም የኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ለኢኮኖሚ ልማት እንዳትጠቀም የሚገድቡ እንደነበሩም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የራሷን ሀብት የማልማት መብት ግብፅ በዓባይ ላይ ያላትን ታሪካዊ ቦታ ለማስጠበቅ ባላት ፍላጎት እንዲሸፈን መደረጉንም ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል።

እንደ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገለጻ፣ የግብፅ ፍላጎት የውሃ ደኅንነት ጉዳይ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባሕር አካባቢ ያለውን ጂኦፖለቲካዊ የኃይል ሚዛን የሚመለከት ነው።

ግብፅ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገትና እያደገ የመጣ ቀጣናዊ ተፅዕኖ እንደ ስትራቴጂያዊ ተግዳሮት እንደምትመለከት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ጥንካሬ ለአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ዓለም አቀፍ የንግድ ግንኙነቷን የሚያሰፋና ቀጣናዊ ኃያልነቷን የሚያሳድግ መሆኑን አብራርተዋል።

ግብጽ የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር መቅረብ የሚያስጨንቃት መሆኑን ያመለከቱት ፕሮፌሰር አለማየሁ፤ የባህር በር ማግኘት ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማጠናከር፣ የገቢና ወጭ ንግድን ለማሳደግ፣ የንግድ ኮሪደሮችን ለማልማትና ጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖዋን ለማሳደግ እንደሚያስችላት ተናግረዋል።

ግብፅ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳታገኝ የምታደርገው ተቃውሞ ሀገሪቷን ከጂኦግራፊ እንድትገለል፣ ኢኮኖሚዋ እንዲገደብና በፖለቲካ ደካማ ለማድረግ የታለመ ጥረት መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ በታሪክ የተመዘገቡ የግብጽ ወታደራዊ ዘመቻዎች በኢትዮጵያ ወታደራዊ የበላይነትና አሸናፊነት ስለተጠናቀቁ፣ ግብጽ ዓላማዋን በቀጥታ በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ማሳካት አልቻለችም።

ሆኖም በቀጣናዊ የፖለቲካ ጥምረትና ግንኙነቶች፣ በተለይም ከኤርትራና ከሱዳን ጋር በመተባበር ጥቅሟን ለማስጠበቅ እየጣረች ትገኛለች ብለዋል።

መሰል የጥምረቱ እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የውስጥ መረጋጋቷን ለማዳከምና በቀጣናው የሚኖራትን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ለማዳከም የታለሙ ናቸው ሲሉም ያብራራሉ።

የኢትዮጵያን ወደቀይ ባህር መቅረብና የባህር በር መልሶ የማግኘት ጥረት ግብጽ በየጊዜው በመቃወምና በጥምረት በመስራት የኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳይሳካ እየሞከረች መሆኑንም ገልጸዋል።

ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት መሆኗ ከጂኦግራፊ ባሻገር የኢኮኖሚ ዕድል፣ በዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓት ውስጥ በሙሉ አቅም እንዳትሳተፍ የሚያደርጋት ነው የሚል መከራከሪያን ያነሳሉ። 

ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ታሪካዊ ግንኙነት ያላትና እስከቅርብ ጊዜ ድረስም የባህር በር ባለቤት እንደነበረች ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።

የባህር በር ማግኘት ኢትዮጵያ የንግድ ግንኙነቷን እንድታሰፋ፣ ኢኮኖሚዋን እንድታጠናክር ብሎም በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ የኢኮኖሚ አቅም በመያዝ በቀይ ባህር ቀጣና ትልቅ ተጽዕኖ እንድታሳድር ያስችላታል ብለዋል።

ፕሮፌሰር አለማየሁ የግብፅ አቋም ተቃርኖ የሚስተዋልበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ አብዛኛው የዓባይ ውሃ ምንጭ የሚገኝባት ብትሆንም ግብፅ  የዓባይን ውሃ የመጠቀም መብት እንዳላት ትናገራለች።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር እንዳትጠጋና የባህር በር እንዳታገኝ ትቃወማለች ሲሉ ተከራክረዋል።

በርካታ ሀገራት በጅቡቲ ወታደራዊ ማዘዣ እንዳላቸው ጠቁመው፤ ይህም  የቀይ ባሕር ቀጣና ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በግብፅ መንግሥትና ሕዝብ መካከል ግልጽ ልዩነት እንዳለ ጠቅሰው፤ የእርሳቸው ትችትም በግብፅ የፖለቲካ አመራር ስትራቴጂያዊ ምኞቶችና ፖሊሲዎች ላይ እንጂ በሕዝቡ ላይ እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ግብፅ የኢትዮጵያን ወደ ቀይ ባሕር መቃረብ መቃወሟና በዓባይ ውሃ ላይ ያላት አቋም እርስ በርስ የተሳሰሩ ብሎም የኢትዮጵያን ልማትና ቀጣናዊ ተፅዕኖ ለመገደብ የሚደረግ ሰፊ ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም