የሉዓላዊነት መከታ- የጀግንነት ምልክት - ኢዜአ አማርኛ
የሉዓላዊነት መከታ- የጀግንነት ምልክት
ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦ የሉዓላዊነት መከታ- የጀግንነት ምልክት
የኢትዮጵያ የጀግንነትና የነፃነት ታሪክ ሲነሳ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ልዩ ስፍራ አለው። የሰራዊቱ የሀገር ፍቅር፣ ለሰንደቁ የሚሰጠው ልዩ ስፍራ እና ለሀገሩ የሚሰጠው ክብር በመስዋዕትነት ጭምር የሚገለፅ ወደር የሌለው ጀግንነት ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የተልዕኮ አፈፃፀሙ፣ ታማኝነቱ፣ ጀግንነቱና ቁርጠኝነቱም መለያዎቹ ሆነው አብረውት ዘልቀዋል። በግዳጅ አፈፃፀም ላይ የሚያሳየው ጽናት፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ተልእኮውን የመፈፀም ብቃቱና ለሀገር ደኅንነት የሚከፍለው መስዋእትነት የጀግንነቱ መገለጫዎች ናቸው።
የሀገር ሉአላዊነት የመጨረሻ መከታ የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ዳር ድንበር በመጠበቅና ለሕዝብ ደኅንነት ሌት ከቀን ዘብ በመሆን በፅናትና ጀግንነቱ ይታወቃል። በምድርም ይሁን በሰማይ የማይደፈር የሚሞክሩት ጠላቶችም ካሉ ድባቅ በመምታት አሳፍሮ የሚመልስ ሰራዊት ነው።
አሁን ላይ የተገነባው ሰራዊትም እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የውጊያ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም የሰማይ ላይ ንስርና የምድር አናብስት መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል። በግዳጅ አፈፃፀም ብቃቱ እና በጀግንነቱ የተመሰከረለት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዛሬም ይሁን ነገ ኢትዮጵያን ለማፅናት በገባው ቃል መሰረት በተግባርም እያረጋገጠ ይገኛል።
በመሆኑም የቴክኖሎጂ እውቀትንና ተቋማዊ አቅምን በመገንባት የዛሬዋንና የወደፊቷን ኢትዮጵያ የሚያስከበር ሰራዊት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተለያዩ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሰማራትም ግዳጁን በላቀ ብቃት በመወጣት ዓለም አቀፍ ከበሬታን ያተረፈ ሰራዊት ነው። በእንዲህ አይነት ተልዕኮ የሰራዊት ሚዛን በጦር ስልት ብቃት ብቻ ሳይሆን በዲሲፕሊን፣ በሕግ ማስከበር፣ በሰብዓዊ ክብር፣ ከህዝብ እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራትን መሰረት ባደረገ መልኩ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ይለካል።
በእነዚህ ሁሉ መለኪያዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የተመሰከረለት ጀግና ሰራዊት ነው። ከጀግንነቱም ባሻገር የሀገር ፍቅር ማሳያ፣ የጥንካሬ መገለጫና የህዝብ አለኝታ መሆኑን በተግባር ያሳየ መሆኑን ሁሉም ይመሰክርለታል። በመሆኑም የሰራዊቱን ጀግንነት ማድነቅ፣ ታሪኩን ማውሳትና ተገቢውን ክብር መስጠት ይገባል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጀግንነቱ የሚጠራ፣ በብቃቱ የተከበረ፣ በሥነ ምግባሩ እየተመሰከረለት መሆኑ እርግጥ ነው። የሀገር መከላከያ ሰራዊት ስሙ እና ተግባሩ በደማቅ ብእር የተፃፈ ነው። በመሆኑም የጀግንነት፣ የቆራጥነት፣ የመልካም ዲሲፕሊን፣ የሀገር ፍቅርና የሕዝብ አገልጋይነት መገለጫዎቹ ለሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ተገቢውን ክብር መስጠት ያስፈልጋል።