በክልሉ እየጣለ ያለው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ እየጣለ ያለው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባል
ዲላ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየጣለ ያለው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራርና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በወቅታዊ የሚቲዮሮሎጂ መረጃ ላይ ተመስርቶ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክት አስተላልፏል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ወገኔ ብዙነህ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በመጠኑም ሆነ በስርጭቱ ከፍተኛ የሆነ ዝናብ እየጣለ መሆኑን የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ ያመላክታል።
እየጣለ ያለውን ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ቀድሞ ከመከላከል ባለፈ ውሃውን ለበጋ ወቅት የመስኖ ልማት ለመጠቀም አርሶና አርብቶ አደሩን በማስተባበር የውሃ እቀባና እርጥበት ማቆያ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አሁን እየጣለ ያለው ዝናብ በተለይ የመኸር እርሻ ዘግይቶ ለገባባቸው የክልሉ አካባቢዎች መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይሁንና በከፍተኛ የዝናብ መጠን አደጋ እንዳይፈጥር ለመከላከል ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን የመጥረግና ሌሎች የአደጋ መከላከል ሥራዎች ማከናወን እንደሚገባ መክረዋል።
በተለይም በተራራማና ተዳፋት አካባቢዎች የአፈር መንሸራተትና የናዳ አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ያለፉ ዓመታት ልምዶች ያሳያሉ ያሉት ኮሚሽነሩ፣ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል የተጀመሩ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ለአብነትም በወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ባስኬቶ እና ጌዴኦ ዞኖች በሚገኙ ከፍተኛ አካባቢዎች የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የጋሞ ዞን፣ አርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደርና የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳን ጨምሮ የደቡብ ኦሞ ዞን አብዛኞቹ የወንዝ ተፋሰስ አካባቢዎች ጎርፍ በሰው፣ በእንስሳትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የመከላከል ስራዎች መጠናከር አለባቸው ብለዋል።
ህብረተሰቡ ኮሚሽኑን ጨምሮ ከፌዴራልና ከክልሉ የሚወርዱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃና ምክረ-ሀሳቦችን በአግባቡ እንዲተገብርም አስገንዝበዋል።
በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የክልሉ ነዋሪዎች የሚሰጡ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን በመከታተል አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡