ቀጥታ፡

የልመናን ታሪክ ያከሰመው የተትረፈረፈ የኢትዮጵያ ግብርና አዲስ የምርታማነት አብዮት!!

መሬት ጦም ማደር የለበትም፤ የልመናን ታሪክ ያከሰመው የተትረፈረፈ የኢትዮጵያ ግብርና አዲስ የምርታማነት አብዮት!!

በሳባ ስለሺ

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ከኢትዮጵያውያን የአኗኗር ሥርዓት ጋር በጥብቅ መስተጋብር የተጋመደ ዘርፍ ነው። የኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ በማሳለጥም ሺህ ዘመናትን አስቆጥሯል። ይሁን እንጂ ተፈጥሮ ከቸረቻት ምቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ተስማሚ የአየር ንብረት ሁኔታ፣ እምቅ የእንስሳት ሀብት እንዲሁም አምራች የሰው ኃይል እንዳላት ሀገር ከመስኩ ማግኘት የሚጠበቅባትን ጥቅም አግኝታለች ለማለት አያስደፍርም።

የአሰራር ክፍተትና የዝናብ ጥገኝነት፣ የቴክኖሎጂና የግብዓት ችግር፣ የተሻሻሉ የፍራፍሬና እንስሳት ዝርያ ተደራሽነት ማነስ ከአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ጋር ተዳምሮ የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት ሲፈትነው ቆይቷል። ይህም በዜጎች የምግብ ዋስትና ላይ ጉልህ ተጽዕኖ በማሳደር ሀገርን የተረጂነት ምሳሌ ሲያደርጋት ቆይቷል።

የኢትዮጵያውያን ለውጥ መሻት በመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የተወለደው የመደመር መንግሥት የሀገርን ዘርፈ ብዙ ስብራቶች ማከም የሚያስችሉ የልማት መርሃ ግብሮችን በመቅረጽ ተግባራዊ አድርጓል። በተለይም በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል ብዝኅ የልማት ዘርፍ የሚመራበትን አቅጣጫ በመተለም ዕድገትን የማፋጠን ሁነኛ መሠረት ጥሏል።

ይህም ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ኢትዮጵያን በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ማሳካት እንደማይቻል የተገነዘበ ታሪካዊ ክስተት ነው። በአምስቱ የብዝኅ ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የተወሰዱ የፖሊሲና የሪፎርም ማሻሻያዎችም የግብርናውን ዘርፍ ዳግም ውልደት እያበሰሩ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “መሬት ጦም ማደር የለበትም፤ ከልመና ራሳችንን መገላገል አለብን፣ ሊታረስና ሊለማ የሚችል መሬት መታረስ አለበት” በሚል ጽኑ እምነት የወሰዱት ቁርጠኛ የልማት ተነሳሽነት የግብርናው ዘርፍ እንዲያንሰራራ አድርጎታል። በዚህም በሁሉም ክልሎች የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ፣ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርና መደበኛ የግብርና ልማት ሥራ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን ቀጥሏል።

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመላክተው፤ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ኢትዮጵያ በዓመት ከ17 ሚሊየን ኩንታል በላይ ስንዴን ከውጭ በማስገባት ከ700 ሚሊየን እስከ 1 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ያስወጣት ነበር። ዛሬ ላይ ግን ይህ የዘመናት ተረጂነት ታሪክ ሆኗል። ምክንያቱም በአርሶና አርብቶ አደሮች ዘንድ የማይታረስ እርሻን የማረስ ባህል በማሳደግ፣ የመስኖና የዝናብ ውሃ አጠቃቃምን በማጎልበት፣ የተሻሻሉ የእንስሳትና የሰብል ዝርያዎችን ተደራሽነት በማስፋት፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ልምድ በማዳበር ምርታማነትን አሳድጓል።

ከስምንት ዓመታት በፊት 50 ሚሊዮን ኩንታል ምርትን መሻገር ተስኖት የቆየው የኢትዮጵያ ስንዴም በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት በሦስቱም የምርት ወቅቶች 8 ነጥብ 47 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በማልማት ከ317 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል። ይህም ተግባር ኢትዮጵያ ከለውጡ ዓመታት በፊት ስንዴን ከውጭ የምታስገባበትን ታሪክ በማስቀረት ፍጆታዋን በሀገር ውስጥ ምርት በማሟላት የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ እመርታዊ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ያመላክታል።

ሌላኛው የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና መሠረት የሆነው የሩዝ ምርት በላቀ የዕድገት ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ሩዝን ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ የማልማት እንቅስቃሴ በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን ቤርአኖ ወረዳ መጀመሩም የመደመር መንግሥት ለሁሉም የግብርና ዘርፍ የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያመላክት ነው። ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባን በይፋ በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት፤ በ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብል ምርት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ኩንታል ደርሷል። ይህም በ2011 ዓ.ም ከነበረው 335 ሚሊዮን ኩንታል ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል።

ቡና ለሀገር ኢኮኖሚ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በሥነ ጽሑፍ ጭምር “የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና፣ ቡና የገቢ ምንጫችን፣ ቡና ቡና የዕድገታችን ገንቢ፣ ቡና ቡና አውታር ነው ቡናችን፣ ቡና ቡና” በሚል ሕብረ ዝማሬ ሲገለጽ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ ቡና ወጪ ንግድ ገቢ ከዓመት ዓመት እመርታዊ ዕድገት እያስመዘገበ ይገኛል። ለአብነትም በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ታሪካዊ ገቢ አግኝታለች። ይህም ገቢ ከባለፉት 17 ዓመታት አጠቃላይ ካገኘችው 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የገቢ መጠን ጋር የተቀራረበ ነው።

የአትክልትና ፍራፍሬም ሌላኛው የግብርና ምርታማነት ዕድገትን እንዲመነደግ ያደረገ ዘርፍ ሆኗል። በተለይም በአረንጓዴ ዐሻራ እና በሌማት ቱርፋት መርሐ ግብር በከተማና ገጠር የተከናወኑ የልማት ተግባራት በአትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነት ላይ አበረታች ውጤት አስግኝተዋል። የአርሶና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አትክልትና ፍራፍሬን በጥራትና በብዛት የማምረት ባህል አሁን ላይ ከዕለት ፍጆታነት የተሻገረ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የገበያ ዕድልን እያሰፋ ይገኛል።

የእንስሳት ልማት ዘርፉም የግብርናን ምርትና ምርታማነት አሳድጓል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ተግባራዊ የተደረገው የሌማት ቱርፋት መርሐ ግብርም የወተትና ሥጋ፣ ዓሳና ማር፣ ዶሮና እንቁላል ምርታማነትን በማሻሻል በከተማና ገጠር የዜጎችን ተመጣጣኝ የምግብና ሥነ-ምግብ ሥርዓት እንዲሻሻል እያደረገ ነው።

በሌላ መልኩም ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች በስፋት ተተክለዋል። በመርሐ ግብሩም እስካሁን ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከሚደረገው ስኬታማ እርምጃ የተሻገረ ዓለም አቀፍ ውጤት ማስገኘቱን ቀጥሏል።

በመደመር መንግሥት በግብርናው መስክ የሚሰሩ ተግባራት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የብልፅግና ግስጋሴ በማነጽ በትክክለኛው የምርታማነት መስመር እንድትጓዝ እያስቻሏትም ነው። በቀጣይም ሁለንተናዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የእርሻ ሜካናይዜሽን ሥርዓትን በማስፋት በሁሉም የግብርና መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን ማላቅ ያስፈልጋል።

በተጨማሪም የአርሶና አርብቶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ጥሬ ዕቃ አቅርቦት ትስስርን በማሳለጥ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም የበለጠ ማጎልበት ይገባል። ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ ለሰነቀችው ኢትዮጵያ ግብርና የልማት መሠረት ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነት፣ የክብርና የብልፅግና መገለጫ ነው። 

የኢትዮጵያን ሀብት በአግባቡ አልምቶ መጠቀም የሕዝብን የሥራ ባህል ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ማጣመርና የምርት አቅምን ማጎልበት፣ የልመና ታሪክን በምርት፣ የጥገኝነት አባዜን በሉዓላዊነት፣ የእጥረት ታሪክን በተትረፈረፈ ምርት መቀየር ይቻላል።

ኢትዮጵያ የሰነቀችው ታላቅ ርዕይ በተግባር እንዲሳካ የግብርና ልማት ከዛሬ የምርት ውጤት ባሻገር የነገውን ትውልድ የሚያኮራ፣ የሚመግብና የሚያኖር ዘላቂ ሀብት ለመፍጠር የሁሉንም የጋራ ትጋት ይጠይቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም