የልማት ዕቅዶች እንዲሳኩ የምናደርገውን ተሳትፎ አጠናክረን እንቀጥላለን - ኢዜአ አማርኛ
የልማት ዕቅዶች እንዲሳኩ የምናደርገውን ተሳትፎ አጠናክረን እንቀጥላለን
ሆሳዕና፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦ መንግስት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የያዛቸው የልማት ዕቅዶች እንዲሳኩ በአካባቢያቸው ልማት የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሀዲያ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ።
"የመደመር መንግስት፣ የህዝብ ድምፅ፣ የጋራ ተሳትፎ፣ የጋራ ልማት!" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
በውይይቱ የተሳተፉ የሀዲያ ዞን ነዋሪዎች፤ መንግስት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የያዛቸው የልማት ግቦች እንዲሳኩ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
ለመንገድ፣ መብራት፣ ንፁህ መጠጥ ውሃ እና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ፍትሀዊ ተደራሽነት ትኩረት እንዲሰጥ የጠየቁት ነዋሪዎቹ ሙስና፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራሮችን መከላከልም በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ተፈራ ጎሪሎ እና ወይዘሮ ሙሉነሽ ሴዲሶ እንዳሉት፤ መንግስት የህዝብ የልማት ፍላጎቶችን ለይቶ ለመፍታት ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ መወያየቱ ለቀጣይ በተያዙ ግቦች ላይ የጋራ መግባባት ይፈጥራል።
የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት የያዛቸው ዕቅዶች ውጤት እንዲያመጡ የልማት ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩም ተናግረዋል።
በተለይ የሆሳዕና ከተማን ለማዘመንና ነዋሪውን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደርና ሌሎች ልማቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የልማት ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።
ወጣት ምስጋና ተረፈ በበኩሉ፤ ወጣቶች በአካባቢያቸው ሰርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በህገ ወጥ ስደት የሚደርስባቸውን እንግልትና ሞት ለማስቀረት የክልሉ መንግስት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
ከመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ህዝብን ለሚጠቅሙ ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ሥራዎች ትኩረት እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
በክልሉ ያሉ ፀጋዎችንና የህዝብን አቅም በማቀናጀት የልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉም አረጋግጠዋል።
አመራሩ የመደመር መንግስት የአገልጋይነት እሳቤን ተላብሶ ለህዝብ ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት መስራት ይኖርበታል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ሙስናን በመከላከልና በልማት ሥራ የህዝብ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል ።
የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግስት ልማትን በፍትሃዊነት ከማረጋገጥ ባለፈ ሌብነትና ብልሹ አሰራሮች ለማረም በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የክልሉን የልማት አቅሞችና ዕድሎችን ወደውጤት መቀየር ወሳኝ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም እንዲሳካ ሁሉም የክልሉ ነዋሪ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ በሀዲያ ዞን የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እና የተለያዩ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።